ኢትዮጵያ ከ128 ዓመት በኋላ ለአድዋ ድል መታሰቢያ የሰራችው ሙዚየም ምን የተለየ ነገር ይዟል?
የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የሆነው የአድዋ ድል ቀን በየዓመቱ የካቲት 23 በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የአስተዳድር ዘመን ለተገኘው ለዚህ ድል እስካሁን ድሉን የሚያስረዳ የራሱ ሙዚየም አልነበረውም
ኢትዮጵያ ከ128 ዓመት በኋላ ለአድዋ ድል መታሰቢያ የሰራችው ሙዚየም ምን የተለየ ነገር ይዟል?
የአድዋ ድል አውሮፓዊያን በበርሊን ጉባኤ ላይ አፍሪካን ተከፋፍለው በቅኝ ግዛት ለመግዛት ሀገራትን በተከፋፈሉት መሰረት ጣልያን ለዚህ ተልዕኮዋ ጦሯን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ሀገራቸውን ከቅኝ ግዛት ያዳኑበት ድል ነው።
128 ዓመት በፊት በተካሄደው ጦርነት የተገኘውን ድል በየዓመቱ የካቲት 23 ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብሩት ቆይተዋል።
ለዚህ ድል መታሰቢያ ከተቀመጡ ማስታወሻዎች መካከል ለድሉ አስተዋጽኦ ያደረጉ የጦር መሪዎች መታሰቢያ ሀውልት እና ተቋማት ስያሜ ባለፈ የራሱ ሙዚየም ሳይሰራለት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን በአዲስ አበባ በተለምዶ ፒያሳ አካባቢ አድዋ ሙዚያም ተሰርቶለታል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የተሰራው ይህ ሙዚየም ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንደተደረገበት መንግስት በይፋ ከመናገር ቢቆጠብም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሙዚየሙ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ዘግቧል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ታከለ ኡማ ግንባታው የተጀመረው ይህ ሙዚየም የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ተመርቋል፡፡
በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ሙዚየም ከምድር በታች ሁለት ደረጃዎችን ጨምሮ 5 ወለል እና 8 በሮች አሉት።
ስምንቱ በሮችም የምሥራቅ ጀግኖች በር፣ የምዕራብ ጀግኖች በር፣ የሰሜን ጀግኖች በር፣ የደቡብ ጀግኖች በር፣ የፈረሰኞች በር፣ የአርበኞች በር፣ የፓን-አፍሪካኒዝም ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
ቅኝ ለመግዛት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው የጣልያን ጦር ጋር በተደረገው ጦርነት ለአድዋ ድል መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ የጦር መሳሪያዎች፣ ወኔ መቀስቀሻ መሳሪያዎች፣ ለጦርነቱ መነሻ የሆኑ ስምምነቶች እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ሁሉ በሙዚየሙ ውስጥ ለእይታ ቀርበዋል፡፡
በሙዚየሙ ውስጥ የጸረ ቅኝ ግዛት ጦርነቱ በድል እንዲቋጭ ያደረጉ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ጀምሮ የጦር መሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ እንስሳት እና ሌሎች ተሳታፊዎች መታሰቢያ ተሰርቶላቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሙዚየሙ በአንድ ጊዜ ከ2 ሺህ እስከ አራት ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችሉ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ መዝናኛ ቤቶች እንዲኖሩት ተደርጎ መገንባቱን የከተማው ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ለለአል ዐይን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡