“ከልዩነታቸው በላይ የህዝብና ሀገርን ቀጣይነት ማየታቸው ነው ኢትዮጵያውያንን ለድል ያበቃችው” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ
“ከልዩነታቸው በላይ የህዝብና ሀገርን ቀጣይነት ማየታቸው ነው ኢትዮጵያውያንን ለድል ያበቃችው” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ
ማንም ያልጠበቀው፣ ለማሰብ እንኳን የሚከብድ ግና በጽናት እና በአንድነት አውን የሆነ፣ እስከዛሬም ድረስ የይቻላል ተምሳሌት ነው፤ የአድዋ ድል፡፡
ከዛሬ 124 ዓመታት በፊት በአድዋ ሰንሰለታማ ተራራዎች ላይ ኢትዮጵያውያን የፈጸሙት ገድል ነጻነቱን ተነጥቆ በቅኝ ግዛት ይማቅቅ ለነበረው መላው የዓለም ጭቁን ህዝብ የድል ብስራትን ያሰማ፣ ስለነጻነት እንዲያስብም ያደረገ ነው፡፡
በየዓመቱ የወቅቱን አርበኞች ገድል በማሰብ የሚከበረው የአድዋ ድል በዓል ዛሬም ለ124ኛ ጊዜ በዋናነት በአድዋና አዲስ አበባ በድምቀት ተከብሯል፡፡
አድዋ በነበረው የበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያውያን በአድዋ ያሳዩት ድል የነጻነት ጮራ እንዲፈነጥቅ ያደረገ ነው፤ ይሄም የጸረ ቅኝ አገዛዝና ጸረ ዘረኝነት ንቅናቄዎችን በመላው ዓለም ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በጊዜው የነበረው ርሀብ (ክፉ ቀን) ቢያሸንፈን ኖሮ አድዋ የድል ምልክት ሳይሆን የውርደት ማቅ ይሆን ነበር ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፣ ነጻነታቸውንና መብታቸውን ለድርድር ያላቀረቡት ቀደምት ኢትዮፕያውያን ትልቅ የሀገራዊ ኩራት ምንጭ ሆነውናል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ የህዝብና ሀገርን ቀጣይነት በወቅቱ በመካከላቸው ከነበረው ልዩነት በላይ ማየታቸው ነው ኢትዮጵያውያንን ለድል ያበቃችው፡፡ ይህ ድል ከተባበርን የማንወጣው አረንቋ እንደሌለ ህያው ምስክር ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ነጻነቷን በማረጋገጥ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች ከመሆንም ባለፈ፣ ዓለማችን አሁን የምትመራባቸውን ህጎች በማጽደቅ ሂደት ከኃያላኑ ጋር የተሳተፈችው በዚሁ በአድዋ ድል ምክንያት መሆኑንም አውስተዋል፡፡
የአድዋ ድል በዓል ስንቸገር ብቻ የምናስታውሰው ጀብዳችን መሆን የለበትም ያሉት ፕሬዝዳንቷ በየቀኑ ተግባራችን ብርታት ሊሆነን ይገባል ሲሉ በመልእክታቸው አንስተዋል፡፡
“የምንኖረው ኢትዮጵያ የምትባል ጀልባ ላይ ነው፤ የጀልባው ተሳፋሪዎችን (የኢትዮጵያውያንን) ደህንነት ማስጠበቅ የምንደራደርበት መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያውያን መደማመጥ ከቻልን እና ለህግ የበላይነት ጸንተን ከቆምን ችግሮቻችንን የማንፈታበት ምክኒያት የለም” ሲሉም ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ክልል ም/ር/መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ደግሞ ህዝቦች ሳይለያዩ በጋራ ከተነሱ ሊገመትና ሊተነበይ የማይችል ድል እንደምናስመዘግብ አድዋ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ለውጭ ጣልቃ ገብነት እጅ እንደማንሰጥ ድሉ ምስክር ነው ያሉት ም/ር/መስተዳድሩ አሁን ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል የአድዋ ጦርነት መንስኤ የሆነውን የውጫሌ ስምምነት በተምሳሌት ልናየው ይገባል ሲሉ መንግስት በሚፈጽማቸው ስምምነቶች ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአሁን ዘመን ቅኝ ገዢዎች፣ ሀገራት የፖሊሲ ነጻነት እንዳይኖራቸው በተለያየ መልኩ የሚሰሩ ናቸው ያሉት ዶ/ር ደብረጽዮን የህዳሴው ግድብ ሰነድም በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባ በዚሁ አጋጣሚ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘመን ተሸጋሪው የአድዋ ድል በዓል በተገቢው መንገድ ሊጠና እና ሊጠበቅ እንደሚገባ በመጠቆም አድዋን ለማልማት የፌደራል መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡
በአድዋ ይገነባል ለተባለው የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ፣ ክልሉ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ መሆኑን በመጠቆም የሚመለከተው ሁሉ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአድዋ በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ድል ነው ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ኮሚሽነር ሃሪሰን ቪክተር ናቸው፡፡
“አድዋ በአፍሪካ ለነፃነት ሲታገሉ ለነበሩ ህዝቦች ትልቅ መልእክት አስተላልፏል፤ የፀረ-አፓርታይድ [የነጮች የበላይነት] ትግልንም በድል ለማጠናቀቅ ጠንካራ ተነሳሽነት ፈጥሯል” ሲሉም ህብረቱን ወክለው አድዋ የተገኙት ሃሪሰን ቪክተር ተናግረዋል፡፡
የአድዋ ድል ለመጪው ትውልድም አስተማሪ ምእራፍ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያውያን በፀረ-ቅኝ ግዛት ያስመዘገቡትን ድል መላው አፍሪካውያን የልማት መሰናክሎችን በማለፍ መድገም ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ በነበረው የአድዋ በዓል አከባበር ላይ ከወትሮው በተለየ በርካታ ህዝብ ተገኝቷል፡፡ በዓሉም ከህጻናት እስከ አዛውንት ባሳዩት የተለያዩ አድዋን የሚዘክሩ ትዕይንቶች እጅግ ደምቆ ነው የተከበረው፡፡
የበዓሉ ታዳሚያን ለዐል-አይን በሰጡት አስተያየት መላው ኢትዮጵያውያን አድዋን መልካም ተምሳሌት በማድረግ፣ ሀገራዊ አንድነቱን ጠብቆ ለላቀ ድል በትጋት ሊረባረቡ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡