ዓለም አቀፍ ለጋሾች ችግር ውስጥ ያለውን የአፋር ህዝብ አልፈው “ትግራይን እንርዳ” ማለታቸው አግባብ አይደለም-የአፋር ክልል
የአፋር ክልል ስድስት ወረዳዎች አሁንም በህወሓት ቁጥጥር ስር በመሆናቸው የተዘረፈውን ሀብት ማወቅ አልተቻለም ተብሏል
“የአፋር ሕዝብ እንደፍየል እና እንደዝንጀሮ በየቦታው ፈሶ እሱን ወደኋላ አድርገን የትግራይ ሕዝብ ብቻ ይረዳ የሚል ቋንቋ ትክክል” አይደለም ሲል የአፋር ክልል በዓለምአቀፍ ለጋሾች ላይ ቅረታውን አቅርቧል፡፡
የአፋር ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሀቢብ እንደገለጹት በአፋር ክልል በርካታ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በየቦታው ነው ያሉት፡፡ የቢሮ ኃላፊው ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች በየቦታው እየወለዱ፤ ለውኃ ጥምና ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላት በአፋር አልፈው ዕርዳታ ለትግራይ ሕዝብ ማድረስ እንደሚፈልጉም የቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ዕርዳታ ማግኘት እንዳለበትና መጎዳት እንደሌለበት እንደሚያምኑ የገለጹት ኃላፊው፤ አፋር ክልል ላይ በችግር ውስጥ የፈሰሰውን ህዝብ ጥሎ ማለፍ ግን አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ያሲን ሀቢብ የአፋር ሕዝብ እንደሌላው ጉልበትና የዓለም ሚዲያ እንደሌለው አንስተው “እኛ ግን የምንችለውን ሁሉ እንሰራለን” ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ ከጤናና ከሰብዓዊነት አንጻር አፋር ክልል ላይ የፈሰሰውን ህዝብ ጥሎ ማለፍ አስቸጋሪ እንደሆነም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
“እኛ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ችግር የለብንም፤ ቢረዳም ችግር የለብንም፤ እኛ የምናየው ከጤናው ረገድ ነው” የሚሉት ኃላፊው የአፋር ሕዝብ ድጋፍ ሳያገኝ እሱን በማለፍ ትግራይን ብቻ እንርዳ የሚለው ጉዳይ “ትንሽ ከእርዳታ አለፍ ያለ ሌላ ነገር ነው የሚመስለው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እሱን እንደክልል መንግስት እየተሰራበት መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በአፋር ክልል አንድ ሆስፒታል፣ 21 ጤና ጣቢያዎች፤ 55 ጤና ኬላዎች በህወሃት ኃይሎች መዘረፋቸውንም የጤና ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በጦርነት ከወደሙት የጤና ተቋማት መካከል 17 ጤና ጣቢያዎች እና 30 ጤና ኬላዎች እንዲሁም አንድ ሆስፒታል ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን የክልል ጤና ቢሮ አስታውቋ፡፡
አሁን ላይ ወደ አገልግሎት የተመለሰው የከልዋን ሆስፒታል ሲሆን ጭፍራ ጤና ጣቢያን ደግሞ ወደ ሆስፒታል ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑም ክልሉ ገልጿል፡፡ እንደክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ገለጻ በአፋር ክልል ስድስት ወረዳዎች በህወሃት ቁጥጥር ስር ስለሆኑ ምን ያህሉ ላይ ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ አልተቻለም፡፡
በአፋር ክልል በህወሃት ቁጥጥር ስር በሚገኙ ወረዳዎች ጦርነት እንደነበረ አል ዐይን አማርኛ በሰመራ ከተማ ተገኝቶ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
አንድ አመት ከሰባት ወር የሞላው በኢትዮጵያ ተቀሰቀሰው ግጭት፤ በሰላም እንዲፈታ አሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት ጥረቶች እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በግጭቱ በትግራይ፣በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው በመፈናቀል ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል ሆኗል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ማንኛውንም የሰላም አማራጭ እንደሚከተል አስታውቆ ነበር፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ለማስቻል የተኩስ አቁም ማወጁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የመንግስትን መግለጫ ተከትሎ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ ወደ ትግራይ የሚገባበት ሁኔታ ከተፈጠረ ተኩስ ለማቆም ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
መንግስት ከግጭት ማቆም ውሳኔው በኋላ ወደ ትግራይ እርዳታ ለማድረስ ቢሞክርም፣ ህወሃት በአፋር ክልል በኩል ያለውን አብአላ መንገድ በመዝጋቱ እርዳታ አለመድረሱን ቀደም ብሎ ጠይቋል፡፡ ህወሓት ግን እርዳታ አልደረሰም እያለ ይገኛል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በዛሬው እለት አፋር ሰመራ የነበሩ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በአብአላ በኩል ወደ ትግራይ መጓጓዛቸውን ገልጿል፡፡