ህወሓት አንድ የአፋር ዞን ተቆጣጥሮ የኢትዮ-ጅቡቲ መስመርን ለመቁረጥ ውጊያ ከፍቷል- አፋር ክልል
ግጭቱን ለመፍታት ህወሓት ከመንግስት ጋር እየተነጋገርኩ ማለቱን መንግስት አስተባብሏል
የህወሓት ኃይሎች በክልሉ የከፈቱትን ጥቃት በመሸሽ ከ300ሺ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል
የአፋር ክልል መንግስት ዛሬ ባውጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች ከታህሳስ 10፣2014 ዓ.ም ጀምሮ በድጋሚ ወደ ክልሉ በመግባት ጥቃት በመክፈት በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን አስታውቋል፡፡
የህወሓት ኃይሎች የክልሉን ሰሜና ዞን ኪልበቲ ረሱ ዞን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው “ሰርዶ ድረስ ዘልቆ በመግባት የኢትዮ-ጂቡቲ መተላለፊያ ኮሪደር ዋና መስመርን ለመቁረጥ” ውጊያ ከፍተዋል ብሏል ክልሉ፡፡
- ህወሓት በሌሎች አካላት በኩል ከመንግስት ጋር ስወያይ ነበር አለ
- ህወሓት “ከመንግስት ጋር በሌሎች አካላት በኩል እየተወያየሁ ነው” ማለቱን መንግስት አስተባበለ
- ከ31አመታት በፊት ደርግ ከህወሓት፤ኦነግና ሻቢያ ጋር ያደረገው ድርድር ለምን ሳይሳካ ቀረ?
መግለጫው በፌደራል መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሓት ኃይሎች በአፍር ክልል በተቆጣጠሯቸው እና ጦርነት እያካሄዱ ባሉባቸው ወረዳዎች ውስጥ ንጹሃን ሰዎች በጅምላ መጨፍጨፋቸውን ጠቅሷል፡፡
የክልሉ መንግስት የህወሓት ኃይሎች በከፈቱት ጦርነት ምክንያት እስካሁን 300ሺ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው የህወሓት ኃይሎች በሰሜን እዝ ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ ነበር፡፡ጦርነቱ ከተጀመረ ከ8 ወር በኋላ የፌደራል መንግስት ጦሩን ከትግራይ ሲያስወጣ የትግራይ ኃይሎች ወደ አፋር እና አማራ ክልል በመግባት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት ማድረሳቸውን የአፋር እና የአማራ ክልል መንግስታት ገልጸዋል፡፡
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ የህወሓት ኃይሎች ተሸንፈው ከሁለቱ ክልሎች መውጣታቸውን መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ነገርግን ህወሓት ከምስራቅ አማራ ከአፋር የወጡት ለሰላም እድል ለመስጠት ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ህወሓት በድጋሚ በተለይ በአፋር በኩል ትንሶሳ እያደረገ መሆኑን እርምጃም እንደሚወስድ በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል ምክንያት ሆኗል፡፡
ህወሓት ግጭቱን ለመፍታት በሌላ አካል በኩል ከመንግስት ጋር ንግግር መጀመሩንና ጥሩ ነገር መኖሩን ቢገልጽም መንግስት ንግግርም ሆነ ድርድርም አለመጀመሩን ገልጿል፡፡