ፖሊስና የእግርኳስ ዳኛዋ ሞሮኳዊ - ቡችራ ካርቡቢ
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዋና ዳኝነት በመሳተፍ በጾታዋ ምክንያት ይደርስባት የነበረውን ጫና ሁሉ አሸንፋ አሳይታለች
ካርቡቢ የወንዶች የአፍሪካ ዋንጫን በመምራት ሁለተኛዋ ሴት አፍሪካዊ ዳኛ ሆናለች
ቡችራ ካርቡቢ ሞሮኳዊት ህግ አስከባሪ ናት። ወንጀለኛ ስታገኝ ካቴናዋን ታወጣለች፤ በሜዳ ላይ ጥፋት ለሚፈጽም ተጫዋች ደግሞ ካርድ ትመዛለች።
“ፖሊስ መሆኔ ሁሌም ፍትህ ለማስፈን እንድሰራ አድርጎኛል” የምትለው ካርቡቢ፥ በኮቲዲቯር አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ የአመታት ህልሟን አሳክታለች።
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እየተሳተፉ ከሚገኙ ስድስት ሴት የዳኞች ቡድን አባላት ውስጥ ብቸኛዋ ጨዋታ የመራች ዋና ዳኛ በመሆንም ታሪክ አጽፋለች።
በምድብ 1 ናይጀሪያ እና ጊኒ ቢሳው ያደረጉትን ጨዋታ መዳኘቷም በሰሜን አፍሪካ ክልል አህጉራዊውን የወንዶች ፍልሚያ በመምራት ቀዳሚዋ አድርጓታል።
ኡጋንዳዊቷ ሳሊማ ሙካንሳንጋ በ2022 በካሜሮን በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በዋና ዳኝነት በመሳተፍ የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊ ዳኛ መሆኗ ይታወሳል።
የ36 አመቷ ፖሊስና የእግር ኳስ ዳኛ ቡችራ ካርቡቢ በኮቲዲቯር በዋና ዳኝነት መሳተፏ ለራሷም ሆነ ለመላው ሴት አፍሪካውያን ዳኞች ትልቅ ድል መሆኑን ለቢቢሲ ተናግራለች።
“በቢሮ ፖሊስ፤ በጨዋታ ሜዳ ዳኛ፤ በቤቴ ደግሞ የሴት ልጅ እናት ነኝ” የምትለው ካርቡቢ፥ በልጅነቷ እግርኳስ ተጫዋች መሆን ብትሻም በሰሜናዊ ሞሮኮ ሜክነስ ከተማ የተጠናከረ የሴት የእግርኳስ ቡድን አለመኖሩ ወደ ዳኝነቱ እንድታዘነብል እንዳደረጋት ትገልጻለች።
ይሁን እንጂ ወንድሞቿን ጨምሮ ቤተሰቦቿ “ወግ አጥባቂ” መሆናቸው በዳኝነት እንዳትገፋ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮባት እንደነበርም ታወሳለች።
በፈረንጆቹ 2007 ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ጨዋታን ስትመራ አባቷ ከተመለከቱ በኋላ ግን ጫናው እየረገበ መሄዱን በመጥቀስም የወደዱትን ነገር ለማድረግ ውስጣዊ ፍላጎት ካለ የማይደረስበት ነገር የለም ትላለች።
በ2020 የወንድ ቡድኖችን ጨዋታ በዋና ዳኝነት በመምራት የመጀመሪያዋ አረብ ሴት ዳኛ መሆን የቻለችው ቡችራ ካርቡቢ፥ ለቪዲዮ ዳኝነት (ቫር) ብቁ በመሆንም የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊ ዳኛ በመሆን ሌላ ታሪክ አጽፋለች።
ሞሮኮ እና ግብጽ በሀገር ውስጥ ሊጎቻቸው የቪዲዮ እገዛ ዳኝነት (ቫር) ተግባራዊ በማድረግ ቀዳሚ ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል።
በሞሮኮ በሚደረጉ የሊግ ጨዋታዎች በቫር ዳኝነት የምትሳተፈው ካርቡቢ፥ “ሴቶች በሁሉም ዘርፍ እንደወንዶች መስራት እንደምንችል እያሳየን ነው፤ ነገር ግን ጥፋት ስናጠፋ ከወንዶቹ በተለየ በጾታችን አስታኮ የመውቀስ የዘመናት ልማዱ አልለቀቀንም” ትላለች።
በአለማቀፍ መድረክ በ2018 እና 2023ቱ የአለም የሴቶች የአለም ዋንጫ በዋኝነት የተሳተፈችው ፖሊስና ዳኛ “ሴቶች ዳኞች የአካል ብቃታቸውን ለማሳደግና የእግርኳስ ህጎችን ጠንቅቀው ለማወቅ ከተጉ የማይቻል ነገር የለም” ባይ ነች።
ሞሮኮ በጥሎ ማለፉ በደቡብ አፍሪካ ተሸንፋ ከኮቲዲቯር ብትሰናበትም በብርቱዋ ሴት ዳኛ ቡችራ ካርቡቢ ስሟ መነሳቱ ቀጥሏል።