ኮቲዲቯር በፊፋ የአለም ሀገራት የእግርኳስ ደረጃ 10 ደረጃዎችን አሻሻለች
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሳ የነበረችው ናይጀሪያም 14 ደረጃዎችን ማሻሻል ችላለች
ኢትዮጵያ በበኩሏ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላ 145ኛ ላይ ተቀምጣለች
የአለም እግርኳስ ማህበር (ፊፋ) የየካቲት ወር የሀገራት የእግርኳስ ደረጃን ይፋ አድርጓል።
አህጉራዊ ውድድሮችን ያደረጉ በርካታ የአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ብሄራዊ ቡድኖችም ደረጃቸውን ማሻሻል ችለዋል።
ባለፈው ሳምንት ያዘጋጀችውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችው ኮቲዲቯር 10 ደረጃዎችን አሻሽላ ከአለም 39ኛ ፤ ከአፍሪካ ደግሞ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በዝሆኖቹ 2 ለ 1 ተሽንፈው ዋንጫውን ያጡት ንስሮቹም 14 ደረጃዎችን በማሻሻል 28ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በሩብ ፍጻሜው በናይጀሪያ የተሸነፈችው አንጎላ በርካታ ደረጃዎችን ከፍ ያለች ሀገር ሆናለች፤ 24 ደረጃዎችን በማሻሻል 93ኛ ደረጃን ይዛለች።
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከምድባቸው ማለፍ ያልቻሉት ቱኒዚያ እና አልጀሪያ በተመሳሳይ 13 ደረጃዎችን ዝቅ ብለው 41ኛ እና 43ኛ ላይ ተቀምጠዋል።
የኮቲዲቯር ቆይታዋ በደቡብ አፍሪካ የተገታው ሞሮኮ በፊፋ የየካቲት ወር የሀገራት የእግርኳስ ደረጃ 1 ደረጃ አሻሽላ 12ኛ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፥ በአፍሪካ 1ኛ ደረጃን እንደያዘች ነው።
የሞሀመድ ሳላህ ሀገር ግብጽ ደግሞ ሶስት ደረጃዎችን ዝቅ ብላ ከአለም 36ኛ ከአፍሪካ 4ኛ ደረጃን ይዛለች።
ሶስት ደረጃዎችን ያሻሻለችው ሴኔጋል በፊፋ የየካቲት ወር የሀገራት የእግርኳስ ደረጃ 17ኛ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፥ ከአፍሪካ ሁለተኛ ሆላነች።
የአፍሪካ ዋንጫውን መስርታ መሳተፍ ግን የከበዳት ኢትዮጵያ በበኩሏ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላ 145ኛ ደረጃን ይዛለች።
የአለም ምርጥ 10 ብሄራዊ ቡድኖች ደረጃ በባለፈው ወር በነበረበት ቀጥሏል፤ አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።