አዘጋጇ ኮትዲቯር 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አነሳች
የ90 ደቂቃው ጨዋታ ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃ ሲቀረው ሰባስቲያን ሀለር ለኮትዲቯር የማሸነፊያዋን እና ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል
የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ያስተናገደችው ኮትዲቯር ናይጄሪያን 2-1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች
የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ያስተናገደችው ኮትዲቯር ናይጄሪያን 2-1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ናይጄሪያ ተከላካዩ ኢኮንግ ጨዋታው በተጀመረ በ38ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ መምራት ችላ ነበር።
ነገርግን በጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ፍራንክ ከሲይ በ62ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረችን ኳስ በጭንቅላቱ ገጭቶ በማስቆጠር ኮትዲቯርን አቻ ማድረግ ቻለ።
የ90 ደቂቃው ጨዋታ ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃ ሲቀረው ሰባስቲያን ሀለር ለኮትዲቯር የማሸነፊያዋን እና ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል።
ጨዋታውን የታደሙት የአለም እግርኳስ ማህበር ፕሬዝደንት ጆቫኒ ቪንሴንዞ ኢንፋንቲኖ ዋንጫውን ለኮትዲቯሩ አምበል አስረክበዋል።
ተጨዋቾቹ በአቢጃን አላሳን ኦታራ ስቴዲየም ከፍተኛ ቁጥር ባለው ደጋፊ ጽምጽ ታጅበው በዋንጨዋው ጨፍረዋል፣ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በውድድሩ የናይጄሪያው ዊሊያምስ ፖውል ትሩሰት ኢኮንግ ኮከብ ተጨዋች፣ የኢኳቶራያል ጊኒው ኢምሊዮ ኑስ ኮከብ ግብ አግቢ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ግብ ጠባቂ ሮንዌን ዊሊያምስ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆነው ተመርጠዋል።
ናይጄሪያ እና ኮትዲቯር ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ከጊኒ ጋር በምድብ አንድ ነበር የተደለደሉት።
ከምድቡ ናይጀሪያ በ7 ነጥብ ከኢኳቶሪያሌ ጊኒ ቀጥሏ በሁለተኛ ደረጃ እና ኮትዲቯር ደግሞ በምርጥ 3ኛ ደረጃ ወደ መጨረሻዎቹ 16ቱ ቡድኖች ውስጥ መካተት ችለዋል።
በምድብ ጨዋታ አፈጻጸም ደስተኛ ያልነበረችው ኮትዲቯር አሰልጣኟን ባሰናበተችበት እለት ነበር ወደ 16ቱ ውስጥ ማለፍ የቻለችው።
በምድብ ስድስት ጨዋታ ሞርኮ ዛምቢያን 1-0 በማሸነፏ ነበር አስተናጋጇ ኮትዲቫር ምርጥ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ አራተኛ የሆነችው።
ናይጄሪያ በጥሎ ማለፍ ካሜሩንን 2-0፣ በሩብ ፍጻሜ አንጎላን 1-0፣ በግማሽ ፍጻሜ ደቡብ አፍሪካን በመለያ ምት 4-2 በማሸነፍ እና ኮትዲቯር ደግሞ በጥሎ ማለፍ ሴኔጋልን በመለያ ምት 4-5፣ በሩብ ፍጻሜ ማሊን 2-1፣ ግማሽ ፍጻሜ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 1-0 በግማሽ ፍጻሜ በማሸነፍ ለዋንጫ ጨዋታ ደርሰዋል።
ትናንት ምሽት ደቡብ አፍሪካ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረጉትን የደረጃ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ አሸንፋ 3ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።
የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ያልተጠበቁ ውጤቶችን አስተናግዷል።
ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት የሞሮኮ፣ የግብጽ፣ የአልጀሪያ፣ የሴኔጋል እና የጋና ቡድኖች አልተሳካላቸውም።