ሴባስቲያን ሃለር ከካንሰር ትግል እስከ አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮናነት…
ሃለር በካንሰር ምክንያት 2 የቀዶ ጥገና እና በርካታ የኬሞቴራፒ ህክምናዎችን አድርጓል

ሴባስቲያን ሃለር ካንሰርን ባሸነፈ በዓመቱ የአፍሪካ ዋንጫን ከሀገሩ ጋር አሸንፏል
በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድንን እና የሀገሪቱን አጥቂ ሴባስቲያን ሃለርን የሚያመሳስል የዳግም መመለስ ታሪኮች ተመዝግበዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኮትዲቯር ካዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመሰናበት ከጫፍ ደርሳ የነበረ ሲሆን፤ ብሄረዊ ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተስፋ አስቆራጭ ነበር።
ሆኖም ግን ምርጥ ሶስተኛ በመሆን ከምድቧ ማለፍ የቻለችው ኮትዲቯር በሚገርም መሻሻል ውስጥ በመድብ ጨዋታ ያሸነፈቻን ናይጄሪያን በፍጻሜ ጨዋታ በመርታት የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን መሆን ችላለች።
የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ሴባስቲያን ሃለርም ከአንድ ዓመት በፊት ከካንሰር ህመም ጋር እየተጋለ ከእግር ኳሱ ዓለም ውጪ ሆኖ እንደነበረ ይታወቃል።
ከካነሰር ጋር እየተጋለ ከአንድ ዓመት በላይ ከእግር ኳስ ርቆ የነበረው አጥቂ ሴባስቲያን ሃለር ከአፍሪካ ዋንጪ ውጪ ሆናለች ተብሎ ተስፋ ተቆርጦባት የነበረችው ሀገሩን የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒን ማድረግ መቻሉ እያነጋገረ ይገኛል።
ከፈረንሳያዊው አባቱ ና ከአይቮሪኮስታዊቷ እናቱ በፈረንሳይ ውስጥ የተወለደው ሴባስቲያን ሃለር፤ በአውሮፓ እግር ኳስ ወስጥ ያደገ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2020 ነበር ለእናተ ሀገሩ ኮትዲቯር ለመጫወትን የመረጠው።
በፈረንጆቹ 2021 አያክስ አምስተርዳምን የተቀላቀለ ሲሆን፤ በመቀጠልም ጉዙው ወደ ጀርመኑ ቦርሺያ ዶርትመንድ ነበር፤ በዚህ ወቅትም በማደግ ላይ የነበረው አጥቂ የነበረው ሃለር የካንስር ታማሚ መሆኑን አወቀ።
በፈረንጆቹ 2022 ሰኔ ወር ላይ ዶክተሮች በዘር ፍሬው ከረጢት ውስጥ የካንሰር እጢ እንዳለ የነገሩት ሲሆን፤ ባለቤቱ ፐሪስላ ስለ ወቅቱ ስታስታውስ “አስደንጋጭ ቅዠት ነበር” በማለት ትገላጸለች።
በመቀጠልም ሃለር ወደ ህክምና የገባ ሲሆን፤ በካንሰር የተጠቃውን የሰውነቱን ከፍል ለማስወገድ በስድስት ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ የቀዶ ጥገና ህክምና እና በርካታ ዙር የኬሞ ቴራፒ ህክምናዎችን ማደረጉም ነው የተነገረው።
በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያትም በእግር ኳስ ላይ ተስፋ ያልቆረጠው ሃለር በሆስፒታል ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያትም ሰይቀር ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቀሴዎችን ያደርግ ነበር።
ካንሰርን ታግሎ ካሸነፈ ከ13 ወራት በኋላም ለእናት ሀገሩ ኮትዲቯር ተመልሶ የመጫወት እድል ያገኘው ሀለር በቁርጭምጭሚት ጉዳት ሳቢያ የምድብ ጨዋታ ውጪ ሆኖም ቆይቶ ነበር።
በእግር ኳሽ ተስፋ መቁረጥን የማያውቀው አጥቂው ሃለር በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ወደ ሜዳ ገብቶ የመጫወት እድል ያገኘው ሲሆን፤ ሁለተኛ አጋማሽ ላይም ሀገሩን አሸናፊ ያደረገች ጎል በማስቆጠርም የሀገሩን የድል ጉዞ ማድመቅ ጀመረ።
በትናትናው እለትም ሀገሩን የዋንጫ አሸናፊ ያደረጋትን የማሸነፊያ ግብ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ማሳረፍ የቻለ ሲሆን፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ የአይቮሪኮስት ዜጎች በደስታ እንዲፈነድቁም ምክንያት መሆን ችሏል።