116 ጎሎች የተቆጠሩበት የኮቲዲቫሩ የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል
ምሽት 5 ስአት በአቢጃን ኮቲዲቯር ከሶስት ጊዜ ሻምፒዮኗ ናይጀሪያ ጋር ትጫወታለች
በምድብ ጨዋታ አዘጋጇን ሀገር ያሸነፈችው ናይጀሪያ ዋንጫውን የማንሳት ቅድመ ግምት ተሰጥቷታል
የአፍሪካ እግርኳስ ሃያላኑን በጊዜ ያሰናበተውና ድንቅ ፉክክር የታየበት 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ምሽት ፍጻሜውን ያገኛል።
በአቢጃን አላሳን ኦታራ ስታዲየም ምሽት 5 ስአት ላይ ኮቲዲቯር ከናይጀሪያ ለዋንጫ ይፋለማሉ።
ደቡብ አፍሪካን በመለያ ምት አሸንፈው ለፍጻሜ የደረሱት ንስሮቹ ለአራተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለመውሰድ ይጫወታሉ።
ከምድባቸው ምርጥ ሶስተኛ ሆነው ወደ ጥሎ ማለፉ የገቡትና ዴሞክራቲክ ሪፐርብሊክ ኮንጎን በመርታት ለፍጻሜ የደረሱት ዝሆኖቹ ደግሞ ከ1992 እና 2015 ድላቸው በኋላ ዋንጫውን በአቢጃን ለማስቀረት ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ።
ናይጀሪያ ከፍጻሜ ተፋላሚዋ ኮቲዲቯር ጋር በምድብ 1 መደልደሏ የሚታወስ ሲሆን፥ ከ24 ቀናት በፊት 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋ በሰባት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፉ መቀላቀሏ አይዘነጋም።
አጀማመራቸው ከፍተኛ ትችት አስከትሎባቸው አሰልጣኛቸውን እስከማሰናበት የደረሱት ዝሆኖቹ ከፈረንጆቹ 2006 (ግብጽ) በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅ ሀገር ሆነው ለፍጻሜ መድረስ ችለዋል።
በአፍሪካ እግርኳስ ቡድኖች ደረጃ ስድስተኛ ላይ የተቀመጠው የናይጀሪያ ብሄራዊ ቡድን በአለማቀፍ ደረጃ 42ኛ ላይ ይገኛል።
የዲዲየር ድሮግባ ሀገር ኮቲዲቯር ደግሞ በአፍሪካ 8ኛ በአለማቀፍ ደረጃ ደግሞ 49ኛ ላይ ተቀምጣለች።
ከ2013 በኋላ ዋንጫውን ለማንሳት የሚፋለሙት ንስሮቹ ካሜሮን፣ አንጎላ እና ደቡብ አፍሪካን አሰናብተው ለፍጻሜ በደረሱበት 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አራተኛውን ዋንጫ እንደሚወስዱ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
በምድብ ጨዋታ በኢኳቶሪያል ጊጊ የ4 ለ 0 ሽንፈት አስተናግደው ሴኔጋልና ማሊን ብሎም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን አሸንፈው ለፍጻሜ የደረሱት ዝሆኖቹም ቀላል ተጋጣሚ ይሆናሉ ተብለው አይጠበቁም።
.እስካሁን 116 ጎሎችን ያስተናገደው የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ጎሎች የተስተናገደበትና ድራማዊ ክስተቶች የታዩበት ምርጥ ውድድር ሆኖ መቆየቱን በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ሲናገሩ ይደመጣል።
ምሽት 5 ስአት ላይ 60 ሺህ ሰዎችን በሚይዘው አላሳን ኦታራ ስታዲየም የሚደረገው የፍጻሜ ፍልሚያም ተጠባቂ ሆኗል።