ስትወሰልት የተያዘች ሚስት በባሏ እርዳታ የምትወደውን ሰው አገባች
የሁለት ልጆቹን እናት የዳረው ባልም በመላው ሕንድ መነጋገሪያ ሆኗል
ሴትዮዋ ከምታፈቅረው ሰው ጋር በትዳሯ ላይ ስትወሰልት የመንደሩ ሰው እጅ ከፍንጅ ይዘዋታል
ስትወሰልት የተያዘች ሚስት በባሏ እርዳታ የምትወደውን ሰው አገባች፡፡
በሀገረ ሕንድ የሚወደድ አንድ ፊልም አለ፡፡ በቦሊውድ የተሰራው ይህ ፊልም “ሁም ዲለ ደ ቹክ ሰናም” በሚል ርዕስ ይታወቃል፡፡ ፊልሙ በመላው ሕንድ የተወደደ ፊልም ሲሆን ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚያፈቅራትን ሴት አግብቶ ይኖር ነበር፡፡ ይሁንና ይህች ሚስቱ ግን ከባሏ ይልቅ ሌላ የምትወደው ሰው ነበር፡፡
ባሏ ለስራ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ እየጠበቀችም ወደዚህ ወደ ምታፈቅረው ሰው ጎራ ትላለች፡፡ የሚስትየው ውስልትናም በመላው የሰፈሩ ሰው የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ባልየው ዘግይቶም ቢሆን ሚስቱ ከእሱ ይልቅ ሌላ የምታፈቅረው ሰው እንዳለ ይረዳል፡፡ የሚያፈቅራት ሚስቱን ለማስደሰት ሲልም ሚስቱን ለምትወደው ሰው ይድራታል፡፡ ይህ ተወዳጅ የነበረው እና በፊልም ገጸ ባህሪ ላይ ብቻ ይታወቅ የነበረው ታሪክ አሁን ወደ እውነትነት መቀየሩን ለየት ያሉ ዘገባዎችን በማስነበብ የሚታወቀው ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
በሕንዷ ቢሃር ግዛት ናረዲጋነጅ መንደር ውስጥ የሚኖሩት እነዚህ ባልና ሚስቶች ከሶስት ዓመት በፊት ተጋብተዋል የተባለ ሲሆን ሁለት ልጆችንም አፍርተዋል፡፡
ይሁንና ይህች ሚስት ባሏ ለስራ ከመንደሩ ወጣ ሲል ወደምታፈቅረው ሰው ጎራ ማለቷ ለባልየው የተሰወረ ቢሆንም በቀዬው ግን ሀገር ያወቀው ጸሀይ የሞቀው ነው ተብሏል፡፡
በሚስትየዋ ድርጊት የተበሳጩ የሰፈሩ ሰዎችም ሚስትየውን እና የሰው ሚስት የሚያባልገውን ሰው እጅ ከፍንጅ ይዘው ለባልየው ያስረክባሉ፡፡
ወስልታለች በተባለችው ሚስቱ እና ሰውየው ላይ እርምጃ ይወስዳል በሚል ይጠበቅ የነበረው ባልም የሁለት ልጆቹን እናት ለምታፈቅረው ሰው ድሯታል ተብሏል፡፡
ሚስቱን መርቆ ሲድር የታየው ተንቀሳቃሽ ምስል በመላው ሕንድ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን ሚስትየው ግን የቀድሞ ባሏን በእንባ ታጅባ ግንባሩን ስማለች ተብሏል፡፡
ይሁንና የሚስትየው እንባ ግን የሀፍረት ይሁን የደስታ እስካሁን አልታወቀም ተብሏል፡፡