በአፍጋኒስታን በተከሰተው ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር ከ2 ሺህ 400 አለፈ
በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 3 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት ከ1 ሺህ 300 በላይ ቤቶችን ማፈራረሱን ታሊባን አስታውቋል
የርዕደ መሬት አደጋው በቱርክ እና ሶሪያ ከደረሱት አስከፊ አደጋዎች የሚመደብ ነው ተብሏል
በአፍጋኒስታን በተከሰተው አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 445 መድረሱን ታሊባን ገለጸ።
በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ሄራት ከተሰኘችው ከተማ በ35 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል ሲለካ 6 ነጥብ 3 ሆኖ ተመዝግቧል።
ቅዳሜ እለት የተከሰተው አደጋ አስከፊነት በዚህ አመት በቱርክ እና ሶሪያ ከደረሱት የርዕደ መሬት አደጋዎች የሚስተካከል ነው ተብሏል።
የአፍጋኒስታን የአደጋ መከላከል ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጃናን ሳይቅ እንዳስታወቁት በርዕደ መሬቱ ከ9 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ስድስት መንደሮችን እንዳልነበሩ አድርጎ ነዋሪዎችን የቀበረው አደጋ 1 ሺህ 320 ቤቶችን ማፍረሱንም ነው ቃል አቀባዩ ለሬውተርስ የተናገሩት።
10 የነፍስ አድን የባለሙያ ቡድኖች አደጋው በደረሰበት የኢራን ድንበር አቅራቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማትረፍ እየተረባረቡ ነው ተብሏል።
በሁለት አስርት አመታቱ ጦርነት ክፉኛ የተጎዳው የአፍጋኒስታን የጤና ስርአት መሰል አደጋ ሲከሰት ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገር የገለጸው የአለም ጤና ድርጅት የጤና ተቋማት ከአቅማቸው በላይ መጨናነቃቸውን አስታውቋል።
እየጎረፈ የሚገኘውን የርዕደ መሬት ተጎጂ ለማስተናገድ በሆስፒታሎች ደጅ ላይ በርካታ አልጋዎች መዘርጋታቸውን የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
ለተጎጂዎች ምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ መድሃኒት እና ልብሶች በፍጥነት እንዲደርስም የታሊባን አስተዳደር የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል።
በተራሮች የተከበበችው አፍጋኒስታን ከፓኪስታን ጋር በምትዋሰንበት ሂንዱ ኩሽ ክልል በተደጋጋሚ የርዕደ መሬት አደጋ ደርሶባታል።