አድማውን ተከትሎ የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዞዎች ተስተጓጉለዋል ተብሏል
የ18 የአፍሪካ ሀገራት የአየር ተቆጣጣሪ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ተገለጸ።
በምዕራብ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ያሉ የአየር ተቆጣጣሪዎች የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ በርካታ በረራዎች መሰረዛቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ በተለይም ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ሊደረጉ የነበሩ በረራዎች ተስተጓጉለዋል ተብሏል።
በተለይም ወደ ቱርክ፣ ፖርቹጋል እና የአሜሪካ ከተሞች ሊደረጉ የነበሩ በረራዎች መራዘማቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት በኑሮ ውድነት መጨመር ምክንያት የደሙወዝ እና ጥቅማጥቅም ይጨመሩልን በሚል ነው።
የሴኔጋል፣ ኮሞሮስ፣ ኮቲዲቯር፣ ካሜሩን፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ማዳጋስካር አውሮፕላን ጣቢያዎች በርካታ በረራዎች የተስተጓጎሉባቸው ስፍራዎች ናቸው።
የስራ ማቆም አድማውን ተከትሎም በረራዎች በመስተጓጎላቸው የየሀገራቱ መንግስት በአድማው የተሳተፉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞችን ማሰራቸው ተገልጿል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የዓለም ነዳጅ እና ምግብ ዋጋ ለመናሩ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ይገለጻል።
የዋጋ መናሩን ተከትሎም በአውሮፓ እና አፍሪካ ያሉ ዜጎች የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ዜጎች እና ተቀጣሪ ሰራተኞች በተለያዩ መንገዶች እየጠየቁ ይገኛሉ።