የብሪታንያ የሰራተኛ ማህበራት ተጨማሪ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ጥምረት ፈጠሩ
ማህበራቱ ጥምረት የፈጠሩት መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ደመወዝ እንዲጨምር ለማድረግ ነው
በብሪታንያ የነዳጅ ወርሃዊ ዋጋ ከአራት ሺህ ዶላር በላይ ደርሷል
የብሪታንያ የሰራተኛ ማህበራት ተጨማሪ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ጥምረት ፈጠሩ፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት ማቅናታቸውን ተከትሎ የዓለም ነዳጅና ምግብ ዋጋ እያሻቀበ ሲሆን፤ ጦርነቱ የዓለምን የምርት አቅርቦት እና የዋጋ መዛነፍን አስከትሏል።
ሩሲያ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት የምትሸፍን ቢሆንም፤ ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን በመጣል መሆናቸውን ተከትሎ በአውሮፓ በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የምርቶች ዋጋ ጨምረዋል።
በዚህና ሌሎች ምክንያቶች በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ እና አቅርቦት በመጨመሩ ዜጎች መንግስቶቻቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ እርምጃዎች እንዲወስዱላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
እያንዳንዳቸው ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ አባል ያላቸው የብሪታንያ ሰራተኛ ማህበራት መንግስታቸው በኑሮ ውድነት ምክንያት ለተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ማስተካካያ እንዲያደርግ ተጸዕኖ ለመፍጠር ሲሞክሩ መቆየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና የብሪታንያ መንግስት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አሁንም ትኩረቱን ለዩክሬን መንግስት ድጋፍ ማድረጉን እንደቀጠለ መሆኑን ማህበራቱ አክለዋል፡፡
አሁን ላይ በብሪታንያ የአንድ ሰው ወርሃዊ የነዳጅ ፍጆታ ከ4 ሺህ ዶላር በላይ መድረሱን የጠቀሱት ማህበራቱ ተጨማሪ የስራ ማቆም አድማዎችን ለማካሄድ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች የኑሮ ውድነቱ ያማረራቸው ዜጎች የስራ ማቆም አድማ በመምታት ላይ ሲሆኑ ከ115 ሺህ በላይ የብሪታንያ ፖስታ ቤት ሰራተኞችም ባሳለፍነው ሳምንት የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ይታወሳል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ የብሪታንያው ፌሊክስቶው ወደብ አገልግሎት ሰራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የስምንት ቀናት አድማ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች ወጪያቸውን ለመቀነስ በሚል የትምህርት ቀናትን አሁን ካለበት ወደ ሶስት ቀናት ዝቅ ለማድረግ ምክክር መጀመራቸው ባሳለፍነው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።
እንዲሁም የሆላንድ የባቡር ትራንስፖርት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
የጀርመኑ ግዙፍ የአቪየሽን ኩባንያ ሉፍታንዛ ሰራተኞችም ደመወዝ እንዲጨመርላቸው በጠሩት የስራ ማቆም አድማ ከአንድ ሺህ በላይ በረራዎቹን መሰረዙ አይዘነጋም።