ካናዳ ያልተከተቡ ተጓዦች ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ መከልከሏን አፍሪካ ሲዲሲ ተቃወመ
በአፍሪካ ካሉ ከ1 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ውስጥ የተከተቡት 16 ሚሊዮን ብቻ ነው
ካናዳ የኮሮና ቫይረስ ያልተከተቡ ተጓዦች ወደ አገሯ እንዳይገቡ አግዳለች
የአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር (ሲዲሲ) የካናዳ መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ ኮንኗል።
ካናዳ የኮሮና ቫይረስ ያልተከተቡ ተጓዦች ወደ አገሯ እንዳይገቡ አግዳለች።
ማዕከሉ የካናዳ መንግስት ያልተከተቡ ዜጎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ የጉዞ እገዳ መጣሏ ዓለም አቀፍ ህግን የተጻረረ ነው ብሏል።
የኮሮና ቫይረስ በፍትሀዊነት ለሁሉም ዜጎች ባልደረሰበት ሁኔታ ያልተከተቡ ዜጎች እንዳይገቡ ማገድ ፍትሀዊ አለመሆኑን ማዕከሉ ገልጿል።
የካናዳ መንግስት ውሳኔ ያስተላለፈው ውሳኔ በተለይም ታዳጊ የአፍሪካ አገራትን የሚጎዳ እና ኢፍትሀዊነተን የሚያበረታታ ነው ብሏል።.
ከዚህ በተጨማሪም የጉዞ እገዳው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኮሮና ቫይረስ መከላከል ትግልን እንደሚያዳክምም የማዕከሉ ዳይሬክተር ጆን ንኬንጋሶንግ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አስጠንቅቋል።
በአፍሪካ እስካሁን ድረስ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የወሰዱ ዜጎች 16 ሚሊዮን ብቻ ሲሆኑ በቀጣዮቹ ወራት 50 ሚሊዮን አፍሪካዊያንን ለመከተብ እቅድ መያዙ ተገልጿል።
በዚህም መክንያት የካናዳ መንግስት ውሳኔ በዋናነት አፍሪካዊያንን ለመጉዳት ያለመ ነው በሚል ተተችቷል።
አፍሪካ አሁን ላይ በሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነች መሆኑን ማዕከሉ አስታውቋል።
በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን በቫይረሱ ከተጠቁት ውስጥም 151 ሺህ 386 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በዚህ በሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁን ላይ የደቡባዊ እና ሰሜናዊ አፍሪካ አገራት ክፉኛ እየተጠቁ ሲሆን ቫይረሱ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በመሰራጨት ላይ ነው ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ ጥቃት እየተፈተኑ ካሉ አገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን እስከዛሬ ድረስ ብቻ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ሲጠቁ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ64 ሺህ በላይ ሆኗል።
ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ በኮሮና ቫይረስ የተጠቃች አገር ሰትሆን ከ541 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በዚህ ቫይረስ ተጠቅተዋል።
ቱኒዝያ በሶስተኛው ዙር ክፉኛ በመጠቃት ላይ ያለች አገር ስትሆን ጎረቤቶቿ ድንበራቸውን በመዝጋት ላይ እንደሆኑ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ግብጽ ኢትዮጵያ እና ሊቢያም ቫይረሱ ቀስ በቀስ እየተሰራጨ ያለባቸው አገራት እንደሆኑ የማዕከሉ የማስጠንቀቂያ ሪፖርት ያስረዳል።