በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ አፍሪካዊያን ቁጥር 105 ሺህ 275 መድረሱን የአፍሪካ ሲዲሲ መረጃዎች አመልክተዋል
የአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል መረጃ ከሆነ በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር ወደ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።
እንደ ማዕከሉ መረጃ ከሆነ በዚህ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ አፍሪካዊያን 105 ሺህ 275 ሲሆን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።
በአፍሪካ ካሉ 55 አገራት ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጎች የተጠቁባቸው አገራት እንደሆኑ ይሄው ማዕከል በሪፖርቱ ገልጿል።
ደቡብ አፍሪካ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ሲያጡ ግብጽ እና ሞሮኮ ደግሞ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎችን የያዙ አገራት ናቸው።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ ከሰሞኑ እንደገለጹት ከሆነ እ.ኤ.አ ከየካቲት 22-28 68ሺ አዳዲስ ኬዞች ሪፖርት መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ በቀዳሚው ሳምንት ሪፖርት ከተደረገው የ9 በመቶ ቅናሽ ያለው ነው፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ከፍተኛ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር የተመዘገበው በደቡባዊ አፍሪካ ነው፡፡ ከአጠቃላዩ አህጉራዊ የአዳዲ ተጠቂዎች ቁጥር የ35 በመቶ ድርሻ አለው፡፡
የሰሜን አፍሪካ ቀጣና 25 በመቶ፣ ምዕራብ አፍሪካ 16፣ ምስራቅ አፍሪካ 18 እና ማዕከላዊ አፍሪካ 7 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም ንኬንጋሶንግ አስቀምጠዋል፡፡
ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር ሪፖርት ያደረጉ ቀዳሚ 5 ሃገራት ደቡብ አፍሪካ (9 ሺ 500 ኬዝ) ፣ ኢትዮጵያ (6 ሺ 200) ፣ ቱኒዚያ (4 ሺ 700)፣ ግብጽ (4 ሺ 200) እና ዛምቢያ (4 ሺ) ናቸው ምንም እንኳን ዳይሬክተሩ መግለጫውን ከሰጡ ወዲህ የቁጥር ልዩነቶች ቢኖሩም፡፡
አጠቃላይ የቫይረሱን የስርጭት ሁኔታ በተለይም በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎችን ቁጥር ስንመለከት ከቀዳሚው ወር በአማካይ የ15 በመቶ ቅናሽ አለው፡፡ በደቡባዊ አፍሪካ የ23 በመቶ፣ ምዕራባዊ አፍሪካ የ16 በመቶ፣ ሰሜናዊ አፍሪካ የ11 በመቶ ቅናሽ አሳይተዋል፡፡
ሆኖም ማዕከላዊ እና ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በቅደም ተከተል የ14 እና የ7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ነው የተነገረው፡፡
ባለፉት 4 ሳምንታት ወይም ባለፈው ወር በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር የ18 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ቅናሹ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባላቸው ሃገራት ጭምር የታየ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የ25 በመቶ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የ18 በመቶ፣ በግብጽ የ1 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ግን አሁንም በቫይረሱ የሚሞቱ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር አልቀነሰም፡፡ በኢትዮጵያ የ7 በመቶ፣ በኬንያ የ6 በመቶ፣ በናይጄሪያ የ10 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ኢትዮጵያ በህንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት የተመረቱ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአስትራ ዜኔካ ክትባቶችን ዛሬ መቀበሏ ይታወሳል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በቅርቡ ክትባቶቹን መስጠት ይጀመራል ያሉ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች፤ የጸጥታ ሀይሎች እና በእድሜ የገፉ ሰዎች ደረጃ በደረጃ ክትባቱን በቅድሚያ እንደሚያገኙም ተገልጿል።