ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የኮሮና ክትባቶችን መስጠት ትጀምራለች
ክትባቶቹ ለቫይረሱ ግንባር ቀደም ተጋላጭ ናቸው ለተባሉ የህክምና ባለሙያዎች ቀድመው ይሰጣሉ ተብሏል
የመጀመሪያ ናቸው ከ2 ሚሊዬን በላይ ክትባቶች ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል
ኢትዮጵያ ዛሬ የመጀመሪያ ናቸው የተባሉ 2 ነጥብ 2 ሚሊዬን የኮሮና ክትባቶችን ተቀብላለች፡፡
ክትባቶቹ አስትራዜናካ በተሰኘው መድሃኒት አምራች ኩባንያ ተዘጋጅተው በህንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት የተመረቱ እና በሃገራት የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) በኩል በተቋቋመው ኮቫክስ የግዢ ስርዓት የተገኙ ናቸው፡፡
ክትባቶቹ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተጭነው ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜ የጤና ሚኒስትሯን ዶ/ር ሊያ ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና የሌሎች አጋር አካላት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
የክትባቶቹ መምጣት ለኢትዮጵያ ትልቅ ነገር ነው ያሉት ዶ/ር ሊያ የክትባቶቹ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ለይቶ ባስቀመጠው መሰረት ግንባር ቀደም ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች፣ተጓዳኝ የጤና እክሎች ላሉባቸው ታማሚዎች እና ለሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ክትባቶቹ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ መሰጠት እንደሚጀምሩም ነው የተናገሩት፡፡
ዶ/ር ሊያ በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጹም ሲሆን የክትባቶቹ መምጣት የመከላከልተግባሩን እንደማያስቆምና ስርጭቱን የመግታት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ክትባቶቹ መከላከሉን የማይተኩ መሆኑ ታውቆ አሁንም ጥንቃቄ እንዳይለይም አሳስበዋል፡፡
እስከ ትናንት ምሽት ድረስ 165 ሺ 29 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ የቫይረሱ ጽኑ ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ታማሚዎቹን ለማከም በሚያስችሉ ሁኔታዎች ረገድ እየገጠመው ያለው ችግር ከዐቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ሚኒስቴሩ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡
በአጠቃላይ 137 ሺ 785 ታማሚዎች ያገገሙ ቢሆንም የ2 ሺ 420 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሚኒስቴሩ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡