ኢንተርኔት መዝጋት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያደረሰባቸው የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
በ2023 የኢንተርኔት መዘጋት የአለም ኢኮኖሚን ከ9 ቢሊየን ዶላር በላይ አሳጥቷል
ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ እና ሴኔጋል የኢንተርኔት መዘጋት ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለባቸው የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ናቸው
በ2023 በ25 ሀገራት 196 የኢንተርኔት መቋረጥ ተከስቶ በ747 ሚሊየን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አድርሷል።
ይህም የአለም ምጣኔ ሃብት ላይ የ9 ነጥብ 01 ቢሊየን ዶላር ጉዳት ማድረሱን ነው የቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ የሚያሳየው።
በአፍሪካም በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከ84 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎችን የንግድ፣ የስራ እና የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ያወኩ የኢንተርኔት መቆራረጦች ተከስተዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በ2023 ለ30 ሺህ 785 ስአታት ኢንተርኔት ተቋርጦ የ1 ነጥብ 74 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ መድረሱ ነው የተነገረው።
በአለማቀፍ ደረጃ በ2023 ከተከሰቱት የኢንተርኔት መዝጋት ድርጊቶች ከግማሽ በላዩ በመንግስታት አነሳሽነት የተፈጸሙ ናቸው።
ኢንተርኔትን በመዝጋት የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመቃወም መብትን ማፈን የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑ ተደጋግሞ ቢገለጽም መንግስታት ኢንተርኔት መዝጋትን እየተለማመዱት መጥተዋል።
በአፍሪካ በ2023 የተመዘገቡት የኢንተርኔት ማቋረጥ ሁነቶች አብዛኞቹ ከወታደራዊ የመንግስት ግልበጣዎች ጋር እና ተቃውሞዎች ጋር የተያያዙ ናቸው ተብሏል።
ቶፕ10ቪፒኤን ድረገጽ ኢንተርኔት እና የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመዝጋት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸውን 5 የአፍሪካ ሀገራት ይፋ አድርጓል።
በ2023 በኢንተርኔት መዝጋት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸው 5 የአፍሪካ ሀገራት፦
ደረጃ | ሀገራት | ኢኮኖሚያዊ ጉዳት | የተዘጋው ስአት ርዝማኔ | የተጎዱ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር | አለማቀፍ ደረጃ |
1 | ኢትዮጵያ | 1.59 ቢሊየን ዶላር | 14,910 | 29.8 ሚሊየን | 2 |
2 | አልጀሪያ | 101.9 ሚሊየን ዶላር | 50 | 32.1 ሚሊየን | 8 |
3 | ሴኔጋል | 57.5 ሚሊየን ዶላር | 3,946 | 8.01 ሚሊየን | 9 |
4 | ጊኒ | 47.4 ሚሊየን ዶላር | 3,720 | 4.9 ሚሊየን | 11 |
5 | ሞሪታንያ | 38.5 ሚሊየን ዶላር | 482 | 1.7 ሚሊየን | 13 |