በአፍሪካ ፈጣን ኢንተርኔት ያለባቸው ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
በ2022 ሰባት የአፍሪካ ሀገራት የኢንተርኔት ፍጥነታቸውን አሳድገው የአለም አቀፉን ደረጃ አሻሽለዋል
ሩዋንዳ፣ ማላዊ እና ጂቡቲ ከፍተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት ለውጥ የታየባቸው ሀገራት ናቸው
በአፍሪካ የተንቀሳቃሽ እና ባለገመድ ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት በ2022 ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቡ ተገለጸ።
የኢንተርኔት ፍጥነትን የሚለካው ኦክላ መረጃ እንደሚያሳየው፥ ሰባት የአፍሪካ ሀገራት ያስመዘገቡት ውጤት በአለም አቀፉ ደረጃ ከተቀመጡበት ከአምስት በላይ ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ አስችሏቸዋል።
በ2022 የባለገመድ ኢንተርኔት ፍጥነት ካለፈው አመት በ28 በመቶ እድገት ማሳየቱንም አለም አቀፉ የኢንተርኔት ፍጥነት ደረጃ አውጪ ኦክላ ገልጿል።
ከፍተኛ ለውጥ ካሳዩት ውስጥ ሩዋንዳ በቀዳሚነት ተጠቅሳለች፤ ከአለም አቀፍ ደረጃዋ 47 ደረጃዎችን በማሻሻል።
ለ114 የኢንተርኔት አቅራቢዎች ፈቃድ የሰጠችው ኪጋሊ፥ በኢንተርኔት መሰረተልማት ላይ ያከናወነችው ስራ በአፍሪካ እጅግ ፈጣን ኢንተርኔት ባለቤት አድርጓታል።
በባለገመድ ብሮድባንድ ኢንተርኔት በሰከንድ 38 ሜጋባይት ማውረድ የሚያስችል ኢንተርኔት ያላት ሩዋንዳ በአለም አቀፍ የኢንተርኔት ፍጥነት ደረጃ 103ኛ ላይ ተቀምጣለች።
ከሩዋንዳ በመቀጠል 9 ደረጃዎችን በማሻሻል ከፍተኛ ለውጥ ያሳየችው ማላዊ ናት። በሰከንድ 9 ነጥብ 7 ሜጋባይት ማውረድና 9 ነጥብ 26 ሜጋባይት መጫን የሚያስችል ኢንተርኔት ዘርግታለች።
ጂቡቲ እና ኮንጎም ሰባት ደረጃዎችን ማሻሻላቸውን የገለጸው ኦክላ፥ ሞሪሺየስ፣ ሌሴቶ እና ጊኒ ያሳዩት መሻሻል አምስት ደረጃዎችን ከፍ እንዲሉ ማድረጉን አመላክቷል።
በጂቡቲ በሰከንድ 8 ነጥብ 47 ሜጋባይት ማውረድ የሚያስችል የባለገመድ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተዘርግቷል፤ ይህም ሀገሪቱን በአለም አቀፉ ደረጃ 159ኛ ላይ አስቀምጧታል።
የኢትዮጵያ የባለገመድ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነትም 5 ሜጋባይት በሰከንድ ሆኖ 172ኛ ደረጃን ይዛለች።
የገመድ አልባ ወይም ሞባይል ኢንተርኔት ፍጥነቷም (በሰከንድ 15 ሜጋባይት ማውረድ የሚያስችል) ከአለም ሀገራት 117ኛ ደረጃን እንድትይዝ አድርጓል።
ከባለፈው ወር ወዲህ ግን የኢንተርኔት ፍጥነቱ ቀንሶ 14 ደረጃዎችን ዝቅ ማለቷንም ነው ኦክላ የሚያመላክተው።
የአፍሪካ ሀገራት የኢንተርኔት ፍጥነት እንዲጨምር በኢንተርኔት መሰረት ልማት እና የ4ጂ እኛ 5ጂ ኔትወርክ ማስፋፋት ትልቅ ድርሻ እንደነበረው አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።
እንደ ኤም ቲ ኤን ያሉ ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ለኔትወርክ ማስፋፊያ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ መመደባቸውንም ለዚህ ማሳያ አድርጎ አቅርቦታል።
በሩዋንዳ እንደታየው የቴሌኮም ዘርፉን ወደ ግል የማዞር ሂደት ፉክክርን በማበረታታቱ የአገልግሎት ጥራቱ ከፍ እንዲልና ወጪም እንዲቀንስ ማድረጉንም ነው የጠቀሰው።
ሰባቱ የአፍሪካ ሀገራት አለማቀፍ ደረጃቸውን ያሻሽሉ እንጂ በስታስቲካ መረጃ መሰረት የ2022 ምርጥ 10 ውስጥ የገባችው ሩዋንዳ ብቻ ናት።
10ሩ ፈጣን ኢንተርኔት ያለባቸው የአፍሪካ ሀገራት (በሰከንድ በአማካይ የሚያወርዱት) ዝርዝርም ቀጥሎ ቀርቧል፦
1. ሩዋንዳ - 52.17 ሜጋባይት በሰከንድ
2. ደቡብ አፍሪካ - 28.62
3. ማዳጋስካር - 19.29
4. ናይጀሪያ - 15.37
5. ሲሼልስ - 14.89
6. ሞሪሺየስ - 13.44
7. ቡርኪናፋሶ - 13.43
8. ኬንያ - 12.42
9. ጋና - 11.24
10. ኡጋንዳ - 11.01