ሶስቱ ባለግዙፍ ምጣኔ ሃብት ሃገራት በኮሮና ታማሚዎች ቁጥርም ከአህጉሪቱ ቀዳሚ ናቸው
ሶስቱ ባለግዙፍ ምጣኔ ሃብት ሃገራት በኮሮና ታማሚዎች ቁጥርም ከአህጉሪቱ ቀዳሚ ናቸው
በአህጉሪቱ ያለው አጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር 148 ሺ መድረሱን የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) አስታውቋል፡፡
ማዕከሉ ዛሬ ባወጣው መረጃ በሁሉም የአህጉሪቱ ሃገራት የተከሰተው ወረርሽኙ የ4 ሺ 228 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል ያለ ሲሆን 61 ሺ 808 የቫይረሱ ታማሚዎች አገግመው ከህክምና ተቋማት መውጣታቸውን ገልጿል፡፡
ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እና ናይጄሪያ በታማሚዎች ቁጥር ቀዳሚ ሃገራት ናቸው፡፡ ከአጠቃላይ የአህጉሪቱ ታማሚዎች ቁጥር በድምሩ ከአንድ ሶስተኛ የበለጠውን ድርሻም ይይዛሉ፡፡
በደቡብ አፍሪካ 32 ሺ 700፣ በግብጽ 25 ሺ በናይጄሪያ ደግሞ 10 ሺ 162 በድምሩ 60ሺ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ታመዋል፡፡
በሟቾች ቁጥር ግብጽ ቀዳሚ ነች፡፡ በግብጽ 959 ሰዎች ሞተዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የ683፣ በናይጄሪያ ደግሞ የ287 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ጎረቤት ሃገር ሱዳን የተመዘገበው የሟቾች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ የ286 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ባገገሙ ሰዎች ቁጥርም እነዚሁ ሃገራት ቀዳሚ ናቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካ 16 ሺ 800፣በግብጽ 6 ሺ፣በአልጄሪያ እና በሞሮኮም በቅደም ተከተል 5 ሺ 500 እና 5 ሺ 700 ገደማ ታማሚዎች አገግመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሟቾች ቁጥር ካላቸው ነገር ግን በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የሚሄድ የታማሚዎች ቁጥር እየተመዘገበ ከሚገኝባቸው ሃገራት መካከል አንዷ ነች፡፡
እስካሁን ዛሬ ሪፖርት የተደረገውን ጨምሮ የ12 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን 217 ሰዎች አገግመዋል፡፡
አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺ 257 ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም 1 ሺ 26 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ይገኛሉ፡፡