እስካሁን በትንሹ 320 ነርሶች ኮሮናን ሲያክሙ ሞተዋል
እስካሁን በትንሹ 320 ነርሶች ኮሮናን ሲያክሙ ሞተዋል
73ኛው የዓለም ጤና አመታዊ ጉባዔ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በግንባር ቀደምትነት በመዋጋት ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን በማመስገን ትናንት ተጀምሯል፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት የሚሞቱ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከፍተኛ አደጋን ደቅኗል ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እንቁ ባሏቸው የጤና ባለሙያዎች ላይ አሳሳቢ ስጋት መደቀኑን ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የነርሶች ምክርቤት በስሩ ካሉት ማህበራት አሰባሰበው በሚል ባስቀመጡት መረጃ መሰረትም በአንዳንድ ሃገራት የሚስተዋለው የነርሶቹ የተጠቂነት ቁጥር በ20 በመቶ አሻቅቧል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም በትንሹ 320 ነርሶች ሞተዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ መረጃዎች በወጉ ሊሰበሰቡ ቢችሉ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የድርጅቱ አባል ሃገራት የጤና ባለሙያዎቻቸውን ከወረርሽኙ ሊጠብቁ፣ አስፈላጊውን የህክምና ግብዓቶች ሊያሟሉላቸው እና መረጃዎችን ስርዓት ባለው መልኩ ሊሰበስቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ በነርሶች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ጥቃት አውግዟል፡፡ ሃገራትና መሪዎች ለዚህ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ ይገባልም ብሏል፡፡ ይህንን የጥቃቱ መነሻዎች ምን እንደሆኑ በውል በመለየት እና በቀላሉ የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል ኃላፊነት ባለው መልኩ ባለሙያዎቹን መጠበቅ እንደሚገባም ነው ያሳሰበው፡፡ ለዚህም ከድርጅቱ ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል ያስታወቀም ሲሆን ዓለም አቀፍ አጋርነትና ትብብር እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመላው ዓለም የ6 ሚሊዬን ነርሶች እጥረት አለ፡፡ባለሙያዎቹን ለመጠበቅና ቁጥራቸውን ለማበራከት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወስዶ ካልተሰራም እጥረቱ ከዚህም ሊብስ ይችላል፡፡
በመላው ዓለም ከ28 ሚሊዬን በላይ ነርሶች እንዳሉ ይገመታል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 20 ሚሊዬን ገደማውን እወክላለሁ የሚለው ምክር ቤቱ በ130 ሃገራት በሚገኙ ማህበራት በፌዴሬሽን ያዋቀሩት ነው፡፡
ሁለተኛ ቀኑን የያዘው ጉባዔው ዛሬም ቀጥሎ ይውላል፡፡