ቅርምቱ አቅም የሌላቸው ደሃ ሃገራትን ስጋት ላይ ጥሏል
የዓለም ኃያላን የኮሮና ክትባትን ለማግኘት ቅርምት ላይ ናቸው
ልዕለ ኃያል ነን ባይ የዓለም ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ቀድሞ ለማግኘት ቅርምት ላይ ናቸው፡፡ መድኃኒቱ ተገኝቶ ክትባት የማዘጋጀቱ ሂደት እንዲፈጥን እና የክትባቱ ቀዳሚ ተጠቃሚ ለመሆንም ረብጣ ገንዘቦችን ፈሰስ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ክትባቶቹ ውጤታማ ይሁኑ አይሁኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ነው እንዲህ በመሆን ላይ ያሉት፡፡ ብቸኛው የመዳኛ እና የተቀዛቀዘ ምጣኔ ሃብታቸውን የማነቃቂያ መንገድ ክትባቱ እንደሆነ የተገለጠላቸውም ይመስላል እንደ ሮይተርስ ዘገባ፡፡
አሜሪካ እንዲህ በመሆን ላይ ካሉት ኃያላን ግንባር ቀደሟ ነች፡፡ በግዙፉ የብሪታኒያ መድኃኒት አምራች አስትራ ዜናካ በመዘጋጀት ላይ ያሉ ክትባቶችን ቀድሞ ለማግኘት የሚያስችላትን የ1 ነጥብ 2 ቢሊዬን ዶላር ክፍያም ፈጽማለች፡፡ ክፍያው ክሎሮኪን ያድነኛል በሚል የወባ መድሃኒትን በወሰዱት በፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ የተፈጸመ ነው፡፡
ተቋሙ በተያዘውና በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ሊያመርት ካቀዳቸው አንድ ቢሊዬን ክትባቶች ውስጥ 4 መቶ ሚሊዬኑን ለመውሰድ የተከፈለም ነው ተብሏል፡፡
ክትባቱ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀ ነው፡፡ አምርቶ የመጠቀሙ ፍቃድ ደግሞ ለአስትራ ዜናካ ተሰጥቷል፡፡ በመጪው መስከረም በተለያዩ ዙሮች ለየሃገራቱ መሰጠትም ይጀምራል፡፡
ብሪታኒያም የመጀመሪያውን አንድ መቶ ሚሊዬን ክትባት ቀድማ እንደምታገኝ ይጠበቃል፡፡ በተጠቀሰው ወርሃ መስከረምም 30 ሚሊዬኑን ታገኛለች፡፡
የክትባቱ ቅርምት
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያልተጠበቀ ነው የተባለ የወረርሽኝ ዱብ እዳ የገጠማቸው ኃያላኑ ከዱብ እዳው የሚያመልጡበትን መላ ለመዘየድ በመሯሯጥ ላይ ናቸው፡፡ ለወረርሽኙ የሚሆን መድሃኒትን በክትባትም በሌላ መልክ ለማዘጋጀት ከሚያደርጉት እሽቅድምድም በዘለለ በቶሎ መድኃኒቱን ሊያዘጋጁ ከሚችሉ ሃገራትም ሆነ ተቋማት ቀድመው ለመውሰድ በመጣደፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ እየተስተዋለ ያለው ነገርም ይኸው ነው፡፡ በእርግጥ እስካሁን ለቫይረሱ የሚሆን ወይም ቫይረሱን የሚያድን መድኃኒት አልተገኘም፡፡ ይህ ሁኔታቸው ታዲያ ድሃ ሃገራትን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡
አሜሪካ ‘ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን’ የተሰኘውን ሃገር በቀል የህክምና ግብዓቶች አምራች ተቋም ጨምሮ ‘ሞደርና እና ሳኖፊ’ ከተባለ የፈረንሳይ መድኃኒት አምራች ተቋም ጋር ስምምነትን ከፈጸመች ዋል አደር ብላለች፡፡
እንዲያውም ሳኖፊ በክትባት መልክ ሊያዘጋጅ የሚችለውን መድኃኒት ለአሜሪካ ቀድሞ ለመስጠት ተስማምቷል መባሉ ፈረንሳይን አስቆጥቶ ነበር፡፡ የሃገሪቱ የጤና እና መድኃኒት ባለስልጣናት ከተቋሙ አመራሮች ጋር እንዲመክሩ እስከማስገደድ የደረሰ ጉዳይ እንደ ነበረም ከሰሞነኛው የፍራንስ 24 ዘገባ ለመረዳት ይቻላል፡፡
መቀመጫውን ካምብሪጅ ያደረገው አስትራ ዜናካም ቢሆን ልክ ከአሜሪካ እና እንግሊዝ ጋር እንዳደረገው ሁሉ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር ስምምነት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ከነዚህ ተቋማት መካከልም ክትባቶችን በስፋት በማምረት የሚታወቀው ህንዱ ’ሴረም‘ አንዱ ነው፡፡የ
የክትባቱ ሁኔታ
የክትባቱ የማዳን ነገር ገና በውል ተጨባጭ ሆኖ አልተረጋገጠም፡፡ በሙከራ ሂደት ላይም ነው ያለው፡፡ ጥቂት የሚይባሉ ሙከራዎችም በተለያዩ ሃገራት ተቋማት በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
በአስትራ ዜናካ እየተዘጋጀ ነው የተባለለት ክትባት አንደኛ እና ሁለተኛ የሚባሉ የክሊኒካል ፍተሸ ደረጃዎችን አልፏል፡፡ ፍቃደኛ በሆኑ ጤነኛ እና እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ያለው የጎንዮሽ እና ተያያዥ ጉዳት በተለያዩ የደቡባዊ እንግሊዝ ቤተ ሙከራዎች እየተጠና ነው፡፡ የሙከራ ሂደቱ ጥቅል መረጃ እና ውጤት በአጭር ጊዜ እንደሚደርስም ይጠበቃል፡፡
ቀደም ሲል የተጠቀሱ የአሜሪካና የፈረንሳይ እንዲሁም የቻይና እና የጀርመን ተቋማት ተመሳሳይ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ሙከራ መቼ እውን እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ መድኃኒት የማዘጋጀቱ ሂደት የተለያዩ ደረጃዎችን እንደሚያልፍ የሚጠቅሱ የዘርፉ ጠበብቶችም በትንሹ ከአመት እስከ አመት ከስድስት ወር ሊወስድ እንደሚችል ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡