በአፍሪካ ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና የኢትዮጵያ ተስፋ እና ስጋት ምን ምን ናቸው?
በዚህ የገበያ እድል ኢትዮጵያ በየትኛው ዘርፍ ብትወዳደር የበለጠ አሸናፊ ልትሆን ትችላለች?
የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ መገበያያ ይሆናል የተባለው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የ3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ምርት ድርሻ አለው
በአፍሪካ ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና የኢትዮጵያ ተስፋ እና ስጋት ምን ምን ናቸው?
የአፍሪካ ህብረት በመጋቢት 2010 ላይ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ባደረገው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነበር የአፍሪካ ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ስምምነት የተፈረመው።
ከ55 የህብረቱ አባል ሀገራት ውስጥ በ44 ሀገራት ፊርማ የተቋቋመው ይህ የንግድ መድረክ አሁን ላይ ከኤርትራ ውጪ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ስምምነቱን ፈርመዋል።
ይህ ስምምነት ከዓለም ንግድ ድርጅት ቀጥሎ በርካታ ሀገራት የፈረሙት ሁለተኛው ግዙፍ የንግድ ስምምነትም ነው።
ዋና መቀመጫውን ጋና አክራ ያደረገው ይህ የንግድ ተቋም ኢትዮጵያን ጨምሮ 47 ሀገራት ስምምነቱን ለመተግበር የሀገራቸው ህግ አድርገው እንዳጸደቁት ተገልጿል።
የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ ንግዳቸውን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ለማካሄድ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ ማህበር አባላት የአፍሪካ ነጻ አህጉር አቀፍ የንግድ ስምምነትን ለመተግበር እየተደረጉ ባሉ ዝግጅቶች ዙሪያ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
አስመጪዎች፣ ላኪዎች፣ አማካሪዎች እና መንግስታዊ የሎጅስቲክ ተቋማት በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት የጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ሔለን ረታ እንዳሉት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ለኢትዮጵያ ነጋዴዎች ትልቅ የገበያ እድል፣ አዲስ ልምድ ስጋቶችን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
ይህ የንግድ እድል ለኢትዮጵያ ነጋዴዎች ሰፊ የገበያ እድል ይዞ መጥቷል ዳይሬክተሯ የንግድ ተቋማት ይህን እድል ለመጠቀም በሰፊው ራሳቸውን ለውድድር እንዲያዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል።
ይሁንና አስቀድመው የሚሸጥ ምርቶችን በማምረት ጥሩ ልምድ ያላቸው እንደ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ነጋዴዎችን ለመወዳደር አቅምን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆኑት አብነት በላይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ 80 በመቶ ንግዷን የምታከናውነው ከአፍሪካ ውጪ ከሆኑ ሀገራት ጋር ነው ብለዋል።
አትክልት እና ፍራፍሬ፣ ቡና እና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ኢትዮጵያ በብዛት ወደ ውጭ ሀገራት የምትልካቸው ምርቶች ናቸው ያሉት ስራ አስኪያጇ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን መጨመር ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ኢትዮጵያ በአንጻራዊነት የተሻለ የንግድ ልውውጥ የምታደርግባቸው ሀገራት ሲሆኑ ሞሮኮ፣ ግብጽ እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ምርቶችን ከምታስመጣባቸው የአፍሪካ ሀገራት እንደሆኑም ተገልጿል።
ይሁንና የንግድ መሰረተ ልማቶች አነስተኛ መሆን፣ ተመሳሳይ እና ውስን ምርቶችን መላክ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አለመዘመን እና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር አመቺ የንግድ ስምምነቶችን እያደረገች አለመሆኗ የነጻ ገበያ እድሉን እንዳንጠቀም ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ስራ አስኪጇ. በስጋትነት አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ሀገራት ልትልካቸው የምትችላቸው በርካታ ምርቶች እንዳሉ የሚናገሩት አብነት ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ የኢትዮጵያ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር የአፍሪካ ንግድ ትስስር የአፍሪካ ነጻ ንግድ ማስፋፊያ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ግዛው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ስምምነት በዋናነት በግብርና ምርቶች ንግድ ዘርፍ ለመወዳደር እየተዘጋጀች መሆኗን ተናግረዋል።
ይህን ሰፊ የአፍሪካ ነጻ የንግድ እድል መጠቀም የሚያስችሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማዘጋጀት፣ ላኪዎችን ማደራጀት እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።
የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት የተደራጀ አምራች ኩባንያዎች ያላቸው መሆኑ ኢትዮጵያ የነዚህ ሀገራት ምርቶች ማራገፊያ እና የሀገር ውስጥ ድርጅቶችን ከገበያ ሊያስወጣቸው አይችልም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም " ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ ምርት የለውም፣ አንዱ ሀገር ሊሸጠው የሚፈልገው ምርት የተለያየ በመሆኑ ይህ ችግር አይሆንም" ሲሉም አቶ ሳሙኤል ምላሽ ሰጥተዋል።
"ኢትዮጵያ አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት የሌላቸውን እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬዎች እና የቅባት እህሎችን በስፋት በመላክ ትወዳደራለች" ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክስ አገልግሎት ተቋማት ያላት መሆኑ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ስምምነትን ለመጠቀም ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ተነስቷል።