የኢትዮጵያ የስጋ ንግድ ከዓመት ዓመት እቀነሰ መምጣቱ ተገለጸ
ለመካከለኛው ምስራቅ ብቻ የስጋ ምርቷን የምትልከው ኢትዮጵያ የገበያው ሦስት በመቶ ድርሻን ብቻ ይዛለች ተብሏል
መንግስት ዘርፉን እምቅ አቅም ተረድቼ ለማሳደግ እየሰራሁ ነው ብሏል
የኢትዮጵያ የስጋ ንግድ ከዓመት ዓመት እቀነሰ መምጣቱ ተገለጸ
ኢትዮጵያ ያላት የእንስሳት ሀብት እምቅ ስለመሆኑ ይነገራል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሀገሪቱ ከ140 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ ከብት አላት። ይህም ቁጥር ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚያደርጋት ቢነገርም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቷ ግን እምብዛም ስለመሆኑ መንግስት ያምናል።
ለዚህም እንቅፋት ናቸው የተባሉ ችግሮች እንዳሉ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ተናግሯል። በዋናነት ግን ችግሩ ዘርፉ “በደንብ ትኩረት ተሰጥቶ ስላልተሰራ ነው” የሚሉት ጌዲዮን ይልማ (ዶ/ር) በባለስልጣኑ የስጋ ኤክስፖርት ቁጥጥርና ፈቃድ ሰጭ ከፍተኛ ባለሞያ ናቸው።
የሀገሪቱን ሀብት ሲገልጹም “ኢትዮጵያ የእንስሳት ሀገር ናት” ይላሉ። ከእንስሳት ኮንትሮባንድ መስፋፋት እስከ የተበጣጠሰ አሰራር፤ ከዝርያ ማሻሻል እክል ጠንካራ እስከሆኑ የወጪ ንግድ መስፈርቶች ድረስ የኢትዮጵያ የስጋ ንግድ እንዳያድግ መሰናክሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በዋናነት ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታርና ባህሬን ለመሰሉ ሀገራት ስጋን ትልካለች።
ሆኖም ግን የገበያ ድርሻዋ ሦስት በመቶ ገደማ ብቻ መሆኑን ጌዲዮን ይልማ (ዶ/ር) ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ሀገሪቱ በፍላጎት ልክ ስጋን አምርታ ለውጭ ገበያ ላለማቅረቧ ከሚነሱ ችግሮች መካከል ዋነኛው “የሀላል መስፈርት”ን እንደልብ አለማሟላቷ ነው።
በእስልምና መርህ መሰረት ወይንም የተፈቀደ ምርት ማሟላት ያለበትን የደህንነትና የጤና መስፈርት አሟልቶ የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ቁልፍ ስፍራ እንደሚይዝ የምግብ ደህንነት ባለሞያ የሆኑት ጽጌ እናውጋው ገልጸዋል።
ሆኖም ይህን ለማድረግ ረጅም ሰንሰለት፣ የባለድርሻ አካላት መብዛት እንዲሁም አስገዳጅ የሆነው የ “ሀላል መስፈርት” አንድ እንስሳ ከተወለደበት ቄራ እስከገባበት ድረስ ያለው መረጃ ተሰንዶ አለመገኘት እንቅፋት ናቸው ብለዋል።
ለቄራዎች፣ ለላኪ ኩባንያዎች እንዲሁም ለምርቶች የ“ሀላል ምስክር ወረቀት” የሚሰጠው የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት፤ በሳዑዲ፣ ዱባይና ኳታር እውቅና አግኝቷል።
በዚህም ምክር ቤቱ የሚሰጠው የ“ሀላል ምስክር ወረቀት” ቅቡልነት አለው።
የም/ቤቱ የሀላል ክፍል ኃላፊ ሲራጅ ኢብራሂም (ዶ/ር) ለአል ዐይን ሲናገሩ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ሀላል ምርትን ለማቅረብ ከእንስሳው አስተራረድ፣ ዝግጅት፣ አቀማመጥና አጓጓዝ ድረስ መስፈርቶች መሟላታቸውን ተቆጣጥረው “የሀላል ምስክር ወረቀት” ይሰጣሉ።
ሆኖም ግን ሀገራዊ የአቅም ችግሮች መኖር የስጋ ምርትን ለመላክ እንቅፋት መሆኑን የሚያነሱት ኃላፊው፤ ለአብነትም የእንስሳት በሽታዎችን አለመቆጣጠርና የቄራዎች የደረጃ አለማደግን ጠቅሰዋል።
11 ቄራዎች ያሏት ኢትዮጵያ ለእንስሳት ስጋ ንግድ መዘመንና መስፋት ተግታ እንድትሰራ ጥሪ ቀርቧል።
አሁን ላይ ባለ አሀዛዊ መረጃ መሰረት በዓመት ከስጋ ንግድ 120 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ይገኛል።
መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን በመግለጽ እንስሳት ልማት ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ማቋቋሙን ተናግሯል።
ጌዲዮን ይልማ (ዶ/ር) “የሀላል የስጋ ንግድ” አሁን ያለን የገበያ ድርሻ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሰባት እስከ ዘጠኝ ለማድረስ መታገዱን ለአል አይን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በደህንነት ችግርና በድርቅ ምክንያት እየቀነሰ የመጣውን የስጋ የወጪ ንግድ ከፍ ለማድረግና እንደ ማሌዢያና ቻይና ያሉ አዳዲስ ገበያዎች ለመድረስ ታስቧልም ብለዋል።
የእንስሳት ምዝገባና ልየታ ስርዓት ሙከራው ተገባዶ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑንም ጌዲዮን ይልማ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ይህም ለ“ሀላል ምርት” አስገዳጅ ከሆኑ መስፈርቶች ውስጥ አንድ እንስሳ ከተወለደበት ቄራ እስከገባበት ድረስ የተሰነደ መረጃ እንዲኖረው ያደርጋል ተብሏል።