ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ንግድ ችሮታ (አጎአ) የመመለስ እድሏ ተስፋዋ ምን ያክል ነው?
አሜሪካ በኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ነበር እገዳውን የጣለችው
ኢትዮጵያ የዋሽንግተን እርምጃ ትክክክል አለመሆኑን በመጥቀስ ውሳኔውን መቃወሟ ይታወሳል
ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ንግድ ችሮታ (አጎአ) የመመለስ እድል አላት?
በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት እና ህወሓት መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ነበር አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አጎአ) እድል ያገደችው።
የእግዱ ዋነኛ ምክንያትም በጦርነቱ ምክንያት በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው የሚል ሲሆን ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ውሳኔ ተቃውማም ነበር።
የአጎአ እድል መሰረዝ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የተቀጠሩ ዜጎችን ስራ አጥ በማድረግ በጦርነቱ ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያንን ይጎዳል ስትል ኢትዮጵያ አሜሪካ ውሳኔዋን እንድታጤነው ጠይቃም ነበር።
ይሁንና ዋሸንግተን ኢትዮጵያን ከአጎአ እግድ እስካሁን ያላነሳች ሲሆን የመነሳት እድል ይኖራት ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ጥያቄው በተለይም የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊዎች የሆኑት የፌደራል መንግሥት እና ህወሀት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ጥያቄው እያየለ መጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን በቆይታቸው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት በአሜሪካ እገዳ የተጣለባት አጎአ እድል እንድትመለስ ለዋሸንግተን በይፋ ጥያቄ አቅርባለች? በሚል በመግለጫው ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች ለቃል አቀባዩ አቅርበዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለምም "አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን የአጎአ እድል እገዳ እንድታነሳ ጥያቄው ከቀረበ መቆየቱን ነገር ግን አሁንም እግዱ እንዳልተነሳ ጉዳዩ ተጨማሪ ምክክር እና ውይይት ይፈልጋል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከንም "የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ትግበራ በስምምነቱ መሰረት ከተፈጸመ ኢትዮጵያ ወደ አግዋ እድል ልትመለስ ትችላለች" ማለታቸውንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
አሜሪካ መንግስት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚሰጠው ከቀረጥና ከኮታ ነጻ የሆነው የንግድ ችሮታ (አጎአ) በፈረንጆቹ 2000 ላይ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ገበያዎች ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ እንዲያቀርቡ የሚፈቅድ እድል ሲሆን በየ25 ዓመቱ የሚታደስ ነው።
አሜሪካ ይህን እድል የዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ያለቻቸውን ሀገራት ከእድሉ ታግዳለች።
ኢትዮጵያ ፣ማሊ እና ጊኒ የአግዋ እድል መስፈርቶችን አያሟሉም በሚል በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ከእድሉ የተሰረዙ ሀገራት ናቸው።