ንግድ ባንክና አቢሲኒያ ባንክ፣ ጨምሮ 16 ባንኮች እንደተጭበረበሩ ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ900 ሚሊየን ብር በላይ እንደተጭበረበረ ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ
የኢትዮጵያ ባንኮች በተፈጸመባቸው የማጭበርበር ወንጀሎች ምክንያት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አጥተዋል ተብሏል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 900 ሚሊየን ብር በላይ እንደተጭበረበረ ፍትህ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
የፍትህ ሚኒስቴር በባንኮች ላይ የሚፈጸም የማጭበርበር ወንጀል መንስኤና የአፈፃጸም ዘዴን በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ የሰራውን ጥናት በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው በዚህ ጥናት ከ370 ቢሊየን ብር በላይ በባንኮች ላይ ማጭበርበር ተሞክሮ እንደነበር ተመላክቷል።
ሚኒስቴሩ እንዳሳወቀው በኢትዮጵያ በተለያዩ ባንኮች ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ ብር የምዝበራ ማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሟል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ባንኮች ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ ብር በተለያዩ የማታለያ መንገዶችን በመጠቀም የተጭበረበሩ ሲሆን፤ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን በላይ ብር ደግሞ የመዛግብት ምዝበራ መፈጸሙን ተቋሙ ገልጿል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ጨምሮ የሌሎች የባንክ፣ የፍትህ እና ጸጥታ ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።
በተደረገው የዳሰሳ ጥናትም ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን በላይ የመዛግብት ምዝበራ በባንኮች ላይ መፈጸሙ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
የባንክ ማጭበርበር ከተፈፀመባቸው 16 ባንኮች መካከል 50 በመቶው ወይም 961 ሚሊየን ብሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈፀመ እንደሆነ በዚሁ ጥናት ላይ ተጠቁሟል።
እንዲሁም 17 በመቶው ወይም 329 ሚሊየን ብር የሚጠጋው በአቢሲኒያ ባንክ እንዲሁም 8 ነጥብ 5 በመቶ ወይም 162 ሚሊየን ብር የሚሆነው በኦሮሚያ ባንክ ላይ መፈጸሙ ተገልጿል።
ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፣ በሀሰተኛ ሰነዶች፣ በይለፍ ቃል ስርቆት፣ በሞባይል ባንኪንግ፣ በሂሳብ ደብተር እና በሀዋላ አገልግሎት በኩል በባንኮች ላይ የማጭበርበር ወንጀሉ እየተፈጸመ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈቃዱ ጸጋ በዚሁ ወቅት አክለውም፥ በባንኮች ላይ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
የማጭበርበር ወንጀሎች መፈጸማቸው እየተረጋገጠ ቢሆንም የህዝብ ገንዘብ በሚፈለገው ልክ ማስመለስ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
ጥናቱም በቀጣይ በባንኮች ላይ እየጨመረ የመጣውን የማጭበርበር ወንጀል በጋራ ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል።