በተገባደደው የፈረንጆቹ 2022 ግጭት፣ መፈንቅለ-መንግስትና ድርቅ አፍሪካን ተቆጣጥሯል
በአህጉሪቱ ዴሞክራሲን ለማጠናከር አንዳንድ ስኬቶች ነበሩም ተብሏል
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ምርጫ፣ ድርቅና መፈንቅለ-መንግስት ባለፉት 12 ወራት በአፍሪካ የተከሰቱ አበይት ክስተቶች ናቸው
በተገባደደው የፈረንጆቹ 2022 ግጭቶች እና ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግስቶች በአፍሪካ አህጉር ላይ ማነቆ ሆነው ቀጥለዋል።
ሆኖም በአህጉሪቱ ዴሞክራሲን ለማጠናከር በበርካታ ሀገራት አንዳንድ ስኬቶች ነበሩ ተብሏል።
በጥር ወር በቡርኪናፋሶ የሚገኙ ወታደራዊ መሪዎች ፕሬዝዳንት ሮክ ማርክ ክርስቲያን ካቦሬን ከስልጣን በማባረር በሉቴነንት ኮሎኔል ዳሚባ ተክተዋል።
በአሜሪካ እና በፈረንሳይ የሰለጠነው የ41 ዓመቱ ወታደር መንግስትን በትነው ህገ-መንግስቱን ያገዱት በፈረንጆቹ 2022 ነበር።
ሆኖም በመስከረም ወር ቡርኪናፋሶ ለሁለተኛ ጊዜ መፈንቅለ መንግስት ያጋጠማት ሲሆን፤ ደስታዎችም በአጭር ተቀጭተዋል።
የጦር ኃይሎች ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ መንበሩን ተቆናጠዋል።
አናዱሉ የአፍሪካን 2022 በገመገመበት ዘገባው የኢትዮጵያን የሰሜን ጦርነት አንስቷል።
የሺህዎች ህይወትን የቀጠፈ ነው ያለው ጦርነቱ ለሁለት ዓመታት ዘልቋል። በተገባደደው ዓመት የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ አማጽያን በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ እጅግ የከፋውን ሁኔታ የገጠማቸውም በ2022 ነው።
ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያን ጨምሮ ሀገራት ተከታታይ የዝናብ ወቅት ባለማግኘታቸው ለአካባቢያቸው መተዳደሪያ ምንጭ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በድርቅ ምክንያት መሞታቸው ይታወሳል።
የሶማሊያ መንግስት ለዓመታት ሲዋጋው የነበረው አልሸባብ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም ቀጥሏል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን ያጡ እና በደርዘን የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት ያደረሱ ፈንጂዎች በመንገድ እና በተሽከርካሪዎች ላይ መጠመድ በፈረንጆቹ 2022 ቀጥለዋል።
ዘገባው የሽብር ቡድኖች በሰሜናዊ ናይጄሪያ፣ በሳህል ክልል እና በሰሜን ሞዛምቢክ በማህበረሰቦች ላይ ስቃይ ማድረጋቸውን ቀጥለዋልም ብሏል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ህገ መንግስቱን ጥሰው ሊሆን ይችላል በሚል ከቀረበበባቸው ክስ ነጻ የሆኑትም በተገባደደው 2022 ዓመት ነው።
የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዊልያም ሩቶን አሸናፊነት ያጸደቀውም በመስከረም ወር ነበር።