በ2022 በአፍሪካ የአውሮፓ ወታደራዊ ተሳትፎ መቀነሱ ተገለጸ
ፈረንሳይ ከማሊ ጠቅልላ በወጣችበት አመት የሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ተሳትፎ እንዲቀንስ የሚጠይቁ ሰልፎች ተበራክተውበት ነበር
ጀርመን እና ዴንማርክ ፓሪስን ተከትለው እንደሚወጡ መገለጻቸውም ለሩስያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ምቹ መደላድል ይፈጥራል ተብሏል
በ2022 በአፍሪካ የአውሮፓ ወታደራዊ ተሳትፎ መቀነሱ ተገለጸ።
የፈረንጆቹ 2022 የአውሮፓ ሀገራት ወታደሮች ከአፍሪካ በስፋት የወጡበት አመት ሆኖ ተመዝግቧል።
ፈረንሳይ ወታደሮቿን ከማሊ እንደምታስወጣ በገለጸችበት አመት ሌሎች ሀገራትም ከሳህል ቀጠና ለመውጣት ውሳኔ አሳልፈዋል።
ለዚህም የሩስያ በአካባቢው የፈጠረችው ተጽዕኖ በዋና ምክንያትነት ይነሳል።
በግንቦት ወር 2021 መፈንቅለ መንግስት ያስተናገደችው ማሊ ለአመታት ስትጠይቀው የቆየው የፈረንሳይ ወታደሮች ይውጡልኝ ጥያቄ በዚህ አመት ምላሽ አግኝቷል።
20 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሀገር ከ2012 ወዲህ ሶስት መፈንቅለ መንግስት አስተናግዳለች።
በሀገሪቱ የፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዴንማርክ ወታደሮች በሰላም ማስከበር ቢሰማሩም ሀገሪቱ መረጋጋት ሊሰፍንባት አልቻለም።
በ2021ዱ የመንግስት ግልበጣ ወደ ስልጣን የመጡት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ከሩስያ ጋር ያላቸው ጥብቅ ወዳጅነት የአውሮፓ ወታደሮችን ከባማኮ እንዲወጡ ገፋፍተዋል።
በዚሁ የፈረንጆቹ አመት ግንቦት ወር ላይም በምዕራባውያን ሃይሎች የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግስት ተሞክሮብኛል ሲሉ ተደምጠዋል።
የፈረንሳይን ጨምሮ የሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ወታደሮች ይውጡልን ጥያቄው መነሻ የበጀት ችግር መሆኑ ከፊት ቀድሞ ይነሳ እንጂ የሞስኮ ግፊት ማየሉ ዋነኛው ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ተንታኞች ይገልጻሉ።
የፈረንሳይ መውጣት
በሳህል ቀጠና ለዘጠኝ አመታት የቆየችው ፈረንሳይ ከየካቲት 2022 እስከ ነሃሴ ወታደሮቿን አስወጥታ አጠናቃለች።
በማሊ ከ2 ሺህ 400 በላይ ወታደሮች የነበሯት ፓሪስ ወደ ጎረቤት ኒጀር ወታደሮቿን ማስወጣቷ የባማኮን ወታደራዊ ጁንታ ቢያስደስትም በቀጠናው ሽብርተኝነት እንዲያንሰራራ ሊያደርግ እንደሚችል ተገምቷል።
ባርካኔ በተሰኘው ዘመቻ ማሊን ጨምሮ በቻድ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ እና ሞሪታንያ የሚንቀሳቀሱት የፈረንሳይ ወታደሮች ቀጣይ እጣ ፈንታም ከባማኮው እንደማይለይ ነው የሚገመተው።
የብሪታንያ ስንብት
ፈረንሳይ ከባማኮ መውጣት በጀመረች ሶስተኛው ወር ብሪታንያም 300 ወታደሮቿ ከማሊ ማስወጣቷን ይፋ አድርጋለች።
ከ2020 ጀምሮ በመንግስታቱ ድርጅት ጥላ ስር በሰላም ማስከበር ስራ የቆዩት የብሪታንያ ወታደሮች እንወጡም የሩስያ የግል ወታደሮች አቅራቢው ዋግነር ወደ ባማኮ መዝለቁ ተነግሯል።
በማሊ ወታደሮች የሚፈጸሙት የመንግስት ግልበጣዎች መበራከትም የአውሮፓ ሀገራቱን ወታደሮች ጥረት መና ማስቀረቱ ይነሳል።
የጀርመን ወታደሮች
የፓሪስ ወታደሮች ከማሊ መውጣትን ተከትሎ ከ1 ሺህ በላይ የጀርመን ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መውጫቸውን እየተጠባበቁ ነው ተብሏል።
በርሊን ባለፈው ጥቅምት ወር ወታደሮቼን በ2024 ጠቅልዬ አስወጣለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።
60 የጀርመን ወታደሮች በማሊ መንግስት ትዕዛዝ በነሃሴ ወር ከባማኮ አውሮፕላን ማረፊያ የሎጂስቲክ ጣቢያ እንዲወጡ መደረጉ ቁጣ ቀስቅሷል።
የምድር እና አየር ቅኝት ስራ እንዳያከናውኑ የሚደረግባቸው ጫናም የመውጫ ጊዜያቸውን ሊያሳጥረው እንደሚችል ተገምቷል።
የማሊ ወታደራዊ መንግስት የዴንማርክ ወታደሮችም ባማኮን ለቀው እንዲወጡ በጥብቅ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።
ይህም ወታደሮቻቸውን ሊያሰማሩ የነበሩ እንደ ኖርዌይ፣ ፖርቹጋልና ሀንጋሪ ያሉ ሀገራትን ውሳኔያቸውን ዳግም እንዲያጤኑ ያደርጋቸዋል ተብሏል።
የፈረንሳይ ወታደሮች ከማዕካላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መውጣት
የፈረንጆቹ 2022 ፈረንሳይ በሌላኛዋ የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፕብሊክ የነበሯትን ወታደሮች አስወጥታ ያጠናቀቀችበት አመት ነው።
ከ2013 ጀምሮ 1 ሺህ 600 ወታደሮቿን ወደ ባንጉይ ልካ ሳንጋሪስ በተሰኘ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሳተፈችው ፓሪስ፥ ከማሊ በወጣችበት ተመሳሳይ ምክንያት ወታደሮቿን አስወጥታለች።
ከ2016 ጀምሮ ሀገሪቱን እየመሩ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ፋውስቲን ቶዴራ የሩስያ የጦር አማካሪዎችን መቅጠራቸው ፓሪስን አስቆጥቷል።
ከሩስያው ዋግነር ኩባንያ ጋር የመሰረቱት ግንኙነትም ፈረንሳይ የባንጉይ ተልዕኮዋን እንድታቋርጥ ማድረጉ በምክንያትነት ይነሳል።
የአውሮፓ ህብረት እቅድ
ሩስያ የአውሮፓ ሀገራትን ከምዕራብ አፍሪካ ማስወጣቷ ሽብርተኝነትን ያነግሳል ያለው የአውሮፓ ህብረት በቀጠናው ሶስት የወታደራዊ ተልዕኮዎችን ለማስጀመር አቅዷል።
ተልዕኮዎቹ መሰረታቸውን በቡርኪናፋሶ እና ኒጀር አድርገው የሳህል ቀጠናን ከአልቃይዳና ከአይ ኤስ የሽብር ቡድኖች ለመታደግ ይንቀሳቀሳል ተብሏል።
ህብረቱ በ2025 የራሱን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ለማደራጀትም ማቀዱን ይፋ አድርጓል።
ይሁን እንጂ በማሊ ብቻ ከ1 ሺ በላይ ወታደሮችን በዋግነር በኩል አሰልፋለች የተባለችው ሩስያ ከሳህል ቀጠና ሀገራት ጋር የመሰረተችው ግንኙነት ፈጣን መሆኑ የህብረቱን እቅድ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል እየተባለ ነው።
የአውሮፓ ሀገራት በማሊ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኒጀር እና ሌሎች የቀጠናው ሀገራት ከአስር አመት በላይ ቆይተው የተፈለገውን ውጤት ያለማስመዝገባቸውም ለህብረቱ ቀጣይ እቅድ አሉታዊ አሻራውን ያኖራል የሚሉ ስጋቶችም አሉ።
በአጠቃላይ የአውሮፓ ሀገራት ከምዕራብ አፍሪካ የወጡበት አመት የሞስኮን ተቀባይነት ማሳደጉ ነው የተነገረው።