በ2022 አዲስ ፕሬዝዳንቶችን ያገኙ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ኬንያ፣ ኮሎምቢያ፣ ፊሊፒንስ እና ደቡብ ኮሪያ አዲስ ፕሬዚዳንት ካገኙት ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ
ፈረንሳይ እና አንጎላ መሪዎቻቸውን ዳግም የመረጡ ሲሆን፥ ብራዚልም በሙስና ተጠርጥረው ታስረው የቆዩትን የቀድሞው ፕሬዚዳንቷን መርጣለች
ሊጠናቀቅ የቀናት እድሜ በቀሩት 2022 አለማችን በርካታ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎችን አስተናግዳለች።
ከጎረቤት ኬንያ እና ሶማሊያ አንስቶ በአንጎላ እስከ ብራዚል ፤ ከፊሊፒንስ እስከ ደቡብ ኮሪያ አዳዲስ መሪዎችን ወደ ስልጣን ያመጡ ምርጫዎች ተካሂደዋል።
ኬንያ - ዊሊያም ሩቶ
የምርጫ ማግስት ግርግር የማያጣት ኬንያ፥ በነሃሴ ወር ያደረገችው ምርጫ ዊሊያም ሩቶን ከራኢላ ኦዲንጋ ጋር አፋጧል። በኡሁሩ ኬንያታ ይሁንታን ተሰጥቷቸው የነበሩት ራኢላ ኦዲንጋ ለአምስተኛ ጊዜ ያደረጉት ሙከራ ግን አልተሳካም። 50 ነጥብ 5 ድምጽ ያገኙት ዊሊያም ሩቶ ኦዲንጋን አሸንፈው በመስከረም ወር ቃለመሃላ ፈጽመዋል። ኦዲንጋም ምርጫው ላይ ጥርጣሬያቸውን ገልጸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ጥረት ማድረጋቸው አይዘነጋም። በ2017 ምርጫ ዳግም የተካሄደባት ኬንያ በ2022 የተሻለ ተአማኝነት ያለው ምርጫ አካሂዳለች።
ሶማሊያ - ሀሰን ሼክ ሞሃመድ
የምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ሶማሊያም በፈረንጆቹ ግንቦት 15 2022 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አካሂዳለች። ሞቃዲሾ ለ15 ሳምንታት በተጓተተው ምርጫ የቀድሞውን መሪ ሀሰን ሼክ ሞሃመድ ዳግም መርጣለች። በሶማሊያ የመጨረሻ ድምጽ ከሚሰጡት 328 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት 214ቱ ለሀሰን ሼክ ሞሃመድ ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ከ2017 ጀምሮ ሀገሪቱን የመሩት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ደግሞ 110 ድምጽ በማግኘት መሸነፋቸው ይታወሳል። ከ2012 እስከ 2017 ሶማሊያን የመሩት ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃመድ ዳግም ስልጣናቸውን እንደተቆናጠጡ በአልሸባብ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ አውጀዋል። በዚህም ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ ከሶማሊያ በሚወጡ ዘግባዎች ሲጠቀስ ከርሟል።
አንጎላ - ሎሬንሶ
አንጎላ ለ38 አመታት የመሯት ፕሬዚዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ በ2017 ጡረታ ከወጡ በኋላ በነሃሴ ወር ሁለተኛውን አወዛጋቢ ምርጫ አድርጋለች። የምርጫው ውጤትም በዶሳንቶስ ተመርጠው የአንጎላ የነጻነት ንቅናቄ (ኤም ፒ ኤል ኤ) ሊቀመንበርነትን የተረከቡት ጆአ ሎሬንሶን ዳግም በስልጣን እንዲቆዩ ያደረገ ሆኗል። አንጎላ ከፖርቹጋል ነጻ ከወጣችበት 1975 ጀምሮ ስልጣን ላይ ያለው ገዥው ፓርቲ፥ በጠቅላላ ምርጫው 51 ነጥብ 17 በመቶ ድምጽ አግኝቷል። በምርጫው የአንጎላ ዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲ ዩኒታ 43 ነጥብ 7 በመቶ ድምጽ ቢያገኝም መንግስት መመስረት አላስቻለውም። ዩኒታ የምርጫውን ውጤት አልቀበለውም ማለቱ አንጎላን ውጥረት ውስጥ ከቶ መቆየቱ አይዘነጋም።
ብራዚል - ሉላ ዳ ሲልቫ
ብራዚል በጥቅምት ወር በሁለት ዙር ያደረገችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በ2017 በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩትን ሉላ ዳ ሲልቫ ወደ ስልጣን መልሷል። በምርጫው ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን የተቀዳደሩት ጄር ቦልሲናሮ በጠባብ ልዩነት ተሸንፈዋል። ኮሮናን ቀላል ጉንፋን ነው በሚል ያጣጣሉት ቦልሶናሮ ብራዚልን በወረርሽኑ ክፉኛ እንድትጎዳ ቸል ማለታቸው በምርጫው ነጥብ አስጥሏቸዋል።
በሚሰጧቸው አወዛጋቢ አስተያየቶች ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ተቀራራቢ ናቸው የሚባልላቸው ቦልሶናሮ የአማዞን ጥቅጥቅ ደን እንዲጨፈጨፍ የሚያበረታ ንግግር ማደረጋቸው ይታወሳል። የብራዚላውያንን የውልደት ምጣኔ ዝቅ በማድረግ ድህነትን ለመቀነስ የያዙት አቋምም መነጋገሪያ ነበር። ቦልሶናሮ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለዜጎች የድጎማ ገንዘብ ለመክፈል ቃል መግባታቸው ተቀባይነታቸውን ከፍ ያደረገው ቢመስልም ለድል አላበቃቸውም።
ደቡብ ኮሪያ - ዮን ሱክ የል
የፕሬዝዳንቶችን የስልጣን ቆይታ 5 አመት ብቻ ያደረገችው ደቡብ ኮሪያ በፈረንጆቹ መጋቢት 9 2022 ያደረገችው ምርጫ የተፎካካሪ ፓርቲውን ፒፕል ፖወር ፓርቲ እጩ ዮን ሱክ የል አሸናፊ አድርጓል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሞን ጃይ ኢን ፓርቲ ዴሞክራቲክ ፓርቲ አስቀድሞ በተደረገ የከንቲባዎች ምርጫም ሽንፈት አስተናግዷል። ሙን ጃይ ኢን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ባደረጉት ጥረትና ስልጣን ከያዙ ወዲህ በ58 በመቶ የጨመረው የቤቶች ዋጋ ለፓርቲያቸው ሽንፈት በምክንያትነት ተጠቅሷል።