አል ዐይን አማርኛ የተጠናቀቀው ዓመት ዋና ዋና ክስተቶችን እንደሚከተለው አሰናድቶላችኋል
የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ተጠናቆ አዲሱ 2023 ተጀምሯል፡፡ ባጠናቀቅነው በዚህ የፈረንጆቹ ዓመት ዓለማችን ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት ብዙ የተለዩ ክስተቶችን አስናግዳለች፡፡
አል ዐይን አማርኛ የተጠናቀቀው ዓመት ዋና ዋና ክስተቶችን እንደሚከተለው አሰናድቶላችኋል፡፡
የመጀመሪው እና ትልቁ የ2022 የዓለማችን ክስተት በአውሮፓ ጦርነት መጀመሩ እንደሆነ ኤፒ ባጠናከረው ዘገባ አስነብቧል።
አውሮፓ ላለፉት 80 ዓመታት በአንጻራዊነት ከሌሎቹ አህጉራት ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም በሩሲያ እና ዩክሬን የተጀመረው ጦርነት ብዙ ታሪኮችን ቀይሯል።
ይህን ጦርነት ተከትሎ አውሮፓ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የተመዘገበበት፣ በየዕለቱ የጦርነት ድባቡ ያየለበት እና በታሪክ ከፍተኛው ተፈናቃዮች የተመዘገቡበት አህጉር ሆኗል።
የአሜሪካ እና ቻይና ውዝግብ ሌላኛው በፈረንጆቹ 2022 ዓመት ከነበሩ የዓለማችን አበይት ክስተቶች መካከል ዋነኛው ነው።
ሁለቱ ሀገራት ያላቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት እየሻከረ ቢመጣም የአሜሪካ ምክር ቤት ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን ከጎበኙ በኋላ ግን ተባብሷል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እና ጉዳት መቀነስ በ2022 ከነበሩ ክስተቶች መካከል አንደኛው እንደሆነም ተጠቅሷል።
በኢራን ከሴቶች ሂጃብ አለባበስ ጋር ተያይዞ የተነሳው ተቃውሞ ሌላኛው የተጠናቀቀው የ2022 ዓመት አበይት ክስተት ሆኖ አልፏል።
የብሪታንያ ንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛ ህልፈተ ህይወት ሌላኛው የዓለማችን አበይት ክስተት ሲሆን የዚሁ አካል የሆነው የብሪታንያ ፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የቦሪስ ኮንሰን እንዲሁም ሊዝ ትሩስ ስልጣን መልቀቅ እና የህንድ ዝርያ ያላቸው ሪሺ ሱናክ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ከዓለማችን ክስተቶች መካከል ዋነኞቹ ነበሩ።
በላቲን አሜሪካ ሀገራት የቀኝ ዘመም ፖለቲካ አራማጆች በምርጫ መሸነፋቸው እና በህዝባዊ ዓመጽ ከስልጣን መነሳታቸው የ2022 ተጨማሪ አበይት ክስተቶች ናቸው።
የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች እና በጦርነት የተፈናቀሉ የዓለማችን ዜጎች ቁጥር መጨመርም የተጠናቀቀው ዓመት ከነበሩ አበይት ክስተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በ2022 ዓመት 32 ሚሊዮን ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቤታቸው የተሰደዱ ሲሆን የተፈናቃዮች ቁጥር በ2021 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ13 ሚሊዮን ብልጫ እንዳለው ተመድ ገልጿል።
የዓለም ህዝብ ቁጥር ስምንት ቢሊዮን መድረሱ፣ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢም ፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ መመረጥ፣ የኳታር የዓለም ዋንጫ፣ የስሪላንካ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በ2022 ከነበሩ ዋና ዋና ክስተቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
የታሪካዊው የብራዚል እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ህልፈተ ህይወት ፣ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ መብላትም ሌላኛው የተጠናቀቀው የ2022 አበይት ክስተቶች ናቸው።
ይህ በዚህ እንዳለ በአዲሱ የፈረንጆቹ 2023 ዓመት ውስጥ ምን ምን ሊከሰቱ ይችላሉ የሚሉት ደግሞ የብዙዎች ፍላጎት ነው።
በአዲሱ ዓመት ለዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናር ዋነኛ ምክንያት የሆነው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በስምምነት እንደሚቋጭ ይጠበቃል።
በቀጣዩ ሰኔ እንደሚካሄድ ፕሮግራም የተያዘለት የቱርክ ምርጫ ሌላኛው ተጠባቂ የዓለማችን ክስተት ነው ተብሏል።
ይህ ምርጫ በዓለም ፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉት ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሀን ቀጣይ እጣ ፈንታ እንደሚወስን መታመኑ ምርጫው ከወዲሁ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
የአሜሪካ እና ቻይና ፍጥጫ ወዴት ያመራ ይሆን? የሚለው ጉዳይ ሌላኛው የዓለምን ሁኔታ ከመወሰን አንጻር ተጠባቂ ክስተት መሆኑ አልቀረም።
የአየር ንብረት ለውጥ በዚሁ በአዲሱ 2023 ዓመት ተጠባቂ ሲሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የዜጎች መፈናቀል ተጨማሪ እና ተጠባቂ የዓለማችን ክስተቶች ይሆናሉ።
የአፍሪካ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እና ህዝብ ብዛት ሀገር ናይጀሪያ ከአንድ ወር በኋላ የምታካሂደው ምርጫ ተጠባቂ ክስተት ነው።