በአልጀሪያ የተገነባው የአፍሪካ ግዙፉ መስጂድ ተመረቀ
120 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው መስጂድ በረጅም ሚናራው ከአለማችን ቀዳሚው ሆኗል ተብሏል
የመስጂዱ ግንባታ ሰባት አመት የወስደ ሲሆን 800 ሚሊየን ዶላር ወጪ ጠይቋል
በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚው ከአለም ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን የያዘው የአልጀርስ መስጂድ በይፋ ተመረቀ።
በአልጀሪያ መዲና አልጀርስ የተገነባው ግዙፍ መስጂድ ከትናንት በስቲያ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ታቡኔ በተገኙበት በይፋ መመረቁ ተገልጿል።
ታላቁ የአልጀርስ መስጂድ ለምዕመናን ክፍት የሆነው ከአራት አመት በፊት ነበር።
ይሁን እንጂ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት እና ፕሬዝዳንት ታቡኔ በወረርሽኙ መያዛቸው የመስጂዱን ምርቃት እንዳዘገየው የታንዛኒያው ዘ ሲቲዝን ዘገባ ያወሳል።
ግዙፉ የአልጀርስ መስጂድ በቻይና የግንባታ ተቋራጭ ኩባንያ የተገነባ ሲሆን፥ ለመጠናቀቅ ሰባት አመት ውስዷል።
800 ሚሊየን ዶላው ወጪ ተደርጎበታል የተባለው መስጂድ 120 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል።
ከሄሊኮፕተር ማሳረፊያ ስፍራው ባሻገር ሚሊየን መጽሃፍትን መያዝ የሚችል ግዙፍ ቤተመጽሃፍትም አለው።
መስጂዱ በረጅም (265 ሜትር) ሚናራውም የአለም ክብረወሰን መያዙ ነው የተገለጸው።
የአረብ እና የሰሜን አፍሪካ የህንጻ ጥበብ የተዋሃደበት ግዙፍና ማራኪ መስጂድ በቀድሞው የአልጀሪያ ፕሬዝዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ አማካኝነት ግንባታው መጀመሩ ይታወሳል።
ቡተፍሊካ በአፍሪካ ግዙፉን መስጂድ ገንብቶ በስማቸው የመሰየው ውጥናቸው በ2019 በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከስልጣናቸው በመነሳቸው ሳይሳካ ቀርቷል።