አፍሪካ 980 ሚሊዬን ዜጎቿን ለመከተብ 9 ቢሊዬን ዶላር ትፈልጋለች
በዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) በኩል ክትባቶችን በርካሽ ምናልባትም ከ3 ዶላር ባልበለጠ ዋጋ እንደሚያገኙ ከሚጠበቁ ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወሳል
980 ሚሊዬኑን እስከ መጪው ጥቅምት ድረስ ለመከተብ 1 ነጥብ 5 ቢሊዬን የኮሮና ክትባቶች እንደሚያስፈልጉ ተገምቷል
አፍሪካ በቀጣዮቹ 2 ዓመታት 980 ሚሊዬን ዜጎቿን ለመከተብ 9 ቢሊዬን ዶላር እንደምትፈልግ የአፍሪካ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ አስታወቀ፡፡
አህጉራዊው የፋይናንስ ተቋም ገንዘቡ ክትባቶችን ለመግዛት እና ለ60 በመቶ ያህሉ የአህጉሪቱ ህዝብ ለማድረስ የሚያስፈልግ ነው ብሏል፡፡
የአፍሪካ አጠቃላይ ህዝብ ብዛት 1 ነጥብ 3 ቢሊዬን መድረሱ ይነገራል፡፡ ከዚህም ውስጥ 60 በመቶ ወይም 980 ሚሊዬን ያህሉን ለመከተብም ታስቧል፡፡ ይህ እስከ ቀጣዩ ዓመት ወርሃ ጥቅምት ድረስ የሚሆን ነው፡፡ ይህ ለማድረግም ከ9 ቢሊዬን ዶላር የሚልቅ ወጪን የሚፈልጉ 1 ነጥብ 5 ቢሊዬን የኮሮና ክትባቶች ያስፈልጋሉ ተብሏል፡፡
ገንዘቡ ከተለያዩ አበዳሪ ተቋማት፣እርጥባን እና ከሃገራቱ የገንዘብ ድጎማ እንዲሁም ከራሱ ከባንኩ እንደሚገኝ የሚታሰብ ነው፡፡
ክትባቶቹን በግዜው እና በፍትሃዊነት ለማዳረስ እንደ አህጉር ከአምራች ተቋማት ጋር መደራደሩ እንደሚጠቅም የባንኩ ፕሬዝዳንት በነዲክት ኦራማህ (ፕ/ር) በአህጉሪቱ የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ተዘጋጅቶ በነበረው የኦንላይን ውይይት ላይ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የአህጉሪቱ ሃገራት በነፍስ ወከፍ ግማሽ ቢሊዬን ዶላር መደጎም ይጠበቅባቸዋል፡፡
20 በመቶ ያህሉን የአህጉሪቱን ህዝብ ለመከተብ ለሚያስፈልገው ክትባት ከሚከፈለው 1 ነጥብ 8 ቢሊዬን ዶላር ቅድሚያ ክፍያ በተጨማሪ 4 ቢሊዬን ዶላሩ በዓለም ባንክ የሚሸፈን ነው፡፡
ቀሪውን 2 ነጥብ 8 ቢሊዬን ዶላር ራሱ እንደሚሸፍን ደግሞ ባንኩ አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽ እና ሞሮኮ የሚፈልጉትን የክትባት መጠን በራሳቸው አቅም ለመሸፈን ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ከቻይናው ግዙፍ መድሃኒት አምራች ሲኖፋርም ጋር ግንኙነት በማድረግም ላይ ናቸው፡፡
ኡጋንዳ፣ርዋንዳ እና ኬንያን መሰል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀውን ክትባት ለማግኘት ከአምራቹ አስትራዜና ጋር በመነጋገር ላይ ናቸው፡፡
ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው 92 ሃገራት በዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) በኩል ክትባቶችን በርካሽ ምናልባትም ከ3 ዶላር ባልበለጠ ዋጋ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡
ከነዚህ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡
ጤና ሚኒስቴር ለጤና ባለሙያዎችና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠት 20 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ህዝብ በመጀመሪያ ዙር ለመከተብ ማቀዱን ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡