በአፍሪካ የኮሌራ በሽታ ስርጭት ከመቼውም ግዜ በበለጠ መጨመሩ ተነገረ
ከ2021 ጀምሮ በአህጉሪቷ 350ሺህ ሰዎች ሲያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን አጥተዋል
ኢትዮጵያ ስርጭቱ እየጨመረ ካለባቸው ሀገራት መካከከል አንዷ ናት
በአስቸጋሪ የአየር ጸባይ እና በሕይወት አድን ክትባቶች እጥረት የተነሳ በአፍሪካ የኮሌራ በሽታ ስርጭት ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
ባለፉት 3 አመታት በተለያዩ የአህጉሪቷ ክፍሎች በተከታታይነት የተከሰቱት ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና ድርቅን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ለርሀብ እንዲሁም ለሰዎች መፈናቀል ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡
በደቡባዊ እና ምስራቅ አፍሪካ ከ2021 ጀምሮ 350ሺህ ሰዎች በኮሌራ በሽታ ሲጠቁ 6ሺዎቹ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡
ማላዊ እና ዛምቢያ በታሪካቸው ከፍተኛ የሆነ የበሽታውን ስርጭት እያስተናገዱ ሲሆን፤ ሞዛምቢክ፣ ዚምቧቡየ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ደግሞ በበሽታው ክፉኛ ከተመቱ ሀገራት መካከል ተቀምጠዋል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ እያየለ ያለው የውሀ ወለድ በሽታዎች ስርጭት የአየር ንብረት ለውጥ ለወረርሽኞች መቀስቀስ ያለውን ሚና አመላካች ነው ብሏል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚፈጠሩ የተፈጥሮ አደጋዎችን ምክንያት ዜጎች ንጽህናቸው ያልተጠበቀ የወንዝ እና የጎድጓድ ውሀን እንዲጠቀሙ ተገደዋል፡፡
እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነም አፍሪካ ከሌላው አለም ክፍል 8 እጥፍ የውሀ ወለድ በሽታዎች ሞት የሚከሰትባት አህጉር ናት፡፡
ድንበር የለሽ ዶክተሮችን ጨምሮ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች ስርጭቱን ለመቆጣጠር የሚያስፈልገው ክትባት እጥረት በመኖሩ በሽታው እያደረሰ የሚገኝው ጉዳት እየጨመረ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም ቢልዮን ዶላሮች ፈሰስ እየተደረጉ የሚገኙት ሀብታም ሀገራትን ይነካሉ በተባሉ በሽታዎች ላይ ብቻ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡
አክለውም ‘’ኮሌራ ሰው መግደል የሌለበት ፣በቀላሉ መታከም የሚችል ክትባቱም ለማምረት ቀላል ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት ግን አናሳ ነው’’ ብለዋል።
የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ 15 የአለም ሀገራት በሽታውን ለመከላከል 82 ሚልየን ዶዝ ክትባት እንዲቀርብላቸው መጠየቃቸውን ነገር ግን በድርጅቱ መጋዘኖች ውስጥ የሚገኝው የክትባት መጠን 46 ሚልየን ዶዝ ብቻ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኮሌራ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በደቡብ አሜሪካ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ የተከሰተ ሲሆን በአፍሪካ የሚገኝው ስርጭት ከሁሉም ይከፋል፡፡