በኦሮሚያ ክልል በኮሌራ በሽታ የሰባት ሰዎች ህይወት አለፈ
ከሀምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተቀሰቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ በኦሮሚያ ክልል ከ300 በላይ ሰዎች ተይዘዋል
ተሰራ በተባለ "የዘመቻ ስራ" ወረርሽኙ አሁን ላይ በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው ተብሏል
የኮሌራ በሽታ ኦሮሚያ ክልል ከሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንበት ባሌ ዞን ሦስት ወረዳዎች ከሀምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ መቀስቀሱን የክልሉ ጤና ቢሮል ገልጿል።
ወረርሽኙ ሀረና ቦሎቃ፣ በርበሬ፣ ዶሎመናና ጉራታ ሙሌ በሚባሉ ወረዳዎች ተቀስቅሶ 334 ሰዎች መያዛቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጧል።
በአካባቢዎቹ በበሽታው የሰባት ሰዎች ህይወት እንዳለፈ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ የአደጋ ጤና አስተዳደር ኃላፊ ተስፋዬ ከበበው (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በማህበረሰቡ ውስጥ ሳይታወቅ በወረርሽኙ የሞተ ሊኖር እንደሚችል ኃላፊው ተናግረዋል።
በኮሌራ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው ወይ ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ተስፋዬ ከበበው (ዶ/ር) "[በወረርሽኙ] ሰባት ሰዎች መሞት አልነበረባቸውም" ብለዋል።
"ቁጥሩ አገልግሎቶች እስኪሟሉ፣ የተወሰኑ ጉዳዮች እስከሚሄዱ እንጂ ይህን ያህል መሆን የለበትም" በማለት በክልሉ በኮሌላ የሞቱ ሰዎች ቁጥር "ከፍተኛ" መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት የወረርሽኙን የሞት ምጣኔ በመጥቀስ ጠቁመዋል።
በወረዳዎች ኮሌራ አንድ ወርና ከአንድ ወር በላይ መቆየቱ ተነግሯል።
ኃላፊው አሁን ላይ "ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው" ብለዋል።
በሦስቱ ወረዳዎ (ከበርበሬ ወረዳ በቀር) በላብራቶሪ የተረጋገጠ (የተመዘገበ) ሪፖርት እንደሌለ ተስፋዬ ከበበው (ዶ/ር) የተናገሩ ሲሆን፤ ሪፖርቱ ከቆመ ሁለት ወር ገደማ መድረሱን አስታውቀዋል።
ኃላፊው "በአብዛኛው ተቆጣጥረነዋል" ብለዋል።
ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥረት እንደተደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የዓለም የጤና ድርጅትና የክልሉ ጤና ቢሮ በቅንጅት ሰርተዋል ብለዋል።
ከማስተባበር ጀምሮ ህክምናውን እስከመስጠት ሁሉን በማሳተፍ "የዘመቻ ስራ" ተሰርቷል ብለዋል።
"ታማሚዎችን እንዴት ማከም እና መቆጣጠር እንደሚገባ በአደጋ ጊዜ ምላሽ የሚሰጥ ራሱን የቻለ ኮሚቴ አለ። እስከ ወረዳ ድረስ በጤና ተቋማት ኮሚቴ ተቋቁሞ ውሃ አቅርቦት፣ ንጽህና መጠበቂያ ማቅረብ [ተሰርቷል]፣ በህክምናው ከቅኝት ጀምሮ የኮሌራ ማከሚያ ስፍራዎች ዝግጅት ድረስ ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ተሰርቷል።"
ወረርሽኙ በባሌ ዞን ከተቀሰቀሰባቸው አራት ወረዳዎች መካከል በሦስቱ በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው ቢባልም፤ በአጎራባች ጉጂ ዞን የበሽታው ምልክቶች መታየታቸውን ተስፋዬ ከበበው (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በጉጂ ዞን "ያልተረጋገጠ" አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል ብለዋል ኃላፊው።
"[በቤተ-ሙከራ] ምርመራ ተደርጎ ከተረጋገጠ እናሳውቃለን" ያሉት ኃላፊው፤ እስካሁን ግን ወረርሽኙ ወደ አጎራባች አካባቢዎች ስለመዛመቱ አልተረጋገጠም ብለዋል።
አል ዐይን በሀገሪቱ ሌሎች ክልሎች (ኮሌራ ያለበትን ሁኔታ) ተከስቶ ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ኮሌራ ባክቴሪያ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፤ የተበከሉ ምግቦችንና መጠጦች በመመገብና በመጠጣት የሚከሰት ነው። በባክቴሪያው የተጠቃ ሰው አይነ- ምድር፣ ምግብንና ውሃን በቀላሉ በመበከል በአፋጣኝ እንደሚተላለፍ የህክምና ባለሞያዎች ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ወረርሽኙ "የሀገሪቱን መልካም ገጽታ እንዳያበላሽ" በሚል የመደባበቅ ጥረቶች አሉ የሚል ትችት ይሰነዘራል።