ግዙፏን ሜትሮፖሊታን ከተማ ኒውዮርክን ያስመረሩት አይጦች
በ2023 መጨረሻ የወጡ መረጃዎች በኒውዮርክ 3 ሚልየን አይጦች እንደሚኖሩ ያመላክታሉ
በከተማዋ ያሉት አይጥች መበራከት የፈጠረው ስር የሰደደ ችግር ከንቲባው ልዩ ስብሰባ እንዲጠሩ አስገድዷቸዋል
የአይጥ መንጋ ግዙፏን የአሜሪካ ሜትሮፖሊታን ከተማ ኒውዮርክን እያስጨነቀ ነው።
በከተማዋ የሚርመሰመሱ አይጦች ጉዳይ ለከንቲባዋ እና ለነዋሪዎቿ እራስ ምታት ሆኗል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለመምከር ከንቲባው ኤሪክ አዳምስ ብሔራዊ የአይጥ ጉባኤ እንዲካሄድ ስብሰባ ጠርተዋል፡፡
መስከረም ላይ ይደረጋል በተባለው ስብሰባ ከቦስተን፣ ኒውኦርሊያንስ እና ሲያትል የአይጥ ስፔሻሊስቶች የሚታደሙበት ሲሆን የከተማ አይጦችን ለመውጋት መፍትሄዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የከተማዋ ጤና ተቋማት ከአይጦች እና ከሌሎች ነፍሳት ጋር በተገናኘ የሚከሰተው ሌፕቶስፓይሮሲስ የተሰኝው በሽታ እየተበረካተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ሌፕቶስፓይሮሲስ ከአይጦች እና ከሌሎች እንሳስት በሚወጡ ፈሳሾች ከተበከለ ውሀ፣ አፈር እና ምግብ ጋር በሚኖር ንክኪ የሚፈጠር ባክቴርያ ሲሆን ምልክቶቹ የሆድ ህመም፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣እራስ ምታት እና የጡንቻ ህመም ናቸው፡፡
በ2023 መጨረሻ የወጡ መረጃዎች በኒውዮርክ ከተማ ሶስት ሚልየን አይጦች እንደሚኖሩ ሲጠቁሙ ይህም የአጠቃላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ቁጥር ግማሽ ለመድረስ የተቃረበ ቁጥር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኒውዮርክ 7ሚልዮን 931ሺህ ሰዎች ይኖራሉ።
በከተማዋ ይህን ያክል አይጦች ቢኖርም ኒውዮርክ ከአሜሪካ ከተሞች በአይጦች ብዛት ቀዳሚዋ አይደለችም ይህን ደረጃ ይዛ የምትገኝው ቺካጎ ስትሆን ሁለተኛ ሎስአንጀልስ ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በአለምአቀፍ ደረጃ ያሉ ከተሞችን የተመለከትን እንደሆን የህንዷ ዴሽኖክ ከተማ ቀዳሚዋ ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ የእንግሊዟ ለንደን ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ የፍቅር ከተማ ተብላ የምትጠራው የፓሪስ ነገር ነው በፓሪስ 2ሚልየን 100ሺህ ሰዎቸ ሲኖሩ የአይጦች ቁጥር ደግሞ 6ሚልየንን ይሻገራል፡፡
ይህ ማለት አይበለው እና በአይጦች እና በሰዎች መካከከል ጦርነት ቢነሳ አንድ ፓሪሳዊ ሶስት አይጦችን ይፋለማል እንደማለት ነው።