በአፍሪካ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አህጉሪቱን በዓመት 18 ቢሊዮን ዶላር እያስወጡ ነው - ዊሊያም ሩቶ
የኬኒያው ፕሬዝዳንት በአህጉሪቱ እየተካሄዱ የሚገኙ ግጭቶች በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አመሰቃቅለዋል ብለዋል
ሩቶ ይህን ያሉት በናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ስብሰባ ላይ ነው
በአፍሪካ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አህጉሪቱን በዓመት 18 ቢሊዮን ዶላር እያስወጡ እንደሚገኙ የኬኒያዊ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተናገሩ፡፡
በ2024 ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት 3 ወራት ባጋጠሙ 1 ሺ የሽብር አጋጣሚዎች 4818 ሰዎች መሞታቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ የተለያዩ ክፍሎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተባብሰው መቀጠላቸው ለከፋ ሰብዓዊ ሁኔታ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በአህጉሪቱ በአሁኑ ወቅት 35 ሚሊየን ተፈናቃዮች፣ 8.9 ሚሊየን ስደተኞች፣ 1.1 ሚሊየን ጥገኝነት ጠያቂዎች እና 1 ሚሊየን ሀገር አልባ ዜጎች መኖሪያ መሆኗን ፕሬዝዳንት ሩቶ ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ስብሰባ ላይ ሲሆን በአህጉሪቱ አሳሳቢ ናቸው ያሏቸውን ግጭት እና እያደረሷቸው የሚገኙ ችግሮችን ጠቅሰዋል፡፡
በዴሞክራቲክ ኮንጎ የኤም 23 አማጽያን ይዞታ እየተጠናከረ መምጣት የአካባቢውን አጠቃላይ ሁኔታ አደጋ ላይ ከመጣሉም በላይ በኮንጎ እና በሩዋንዳ መካከል ጦርነት እንዳያስነሳ ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በሳህል ቀጠና እንደ ማሊ፣ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ያሉ ሀገራት ከአልቃይዳ እና ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች መጠናከር ቀጠናውን ሰላም እያናጋ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ በሁለት ወታደራዊ ሀይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ሱዳን ሁኔታም ከመርገብ ይልቅ እየተባባሰ ይገኛል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
እነዚህ እና ሌሎች ያልተጠቀሱ በአፍሪካ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አህጉሪቱን በዓመት 18 ቢሊዮን ዶላር እያሳጡ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የአህጉሪቷ እድገት ሰላምን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
ሩቶ አሁን ያለው የአፍሪካ ህብረት የፀጥታ መዋቅር የአህጉሪቱን ውስብስብ ተለዋዋጭነት እና ተግዳሮቶች ለመፍታት በበቂ የተደራጀ አለመሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቷ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና መፍትሄ ሰጪነት የተበታተነ እንዲሁም ደካማ አቋም ላይ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ የህብረቱ የሰላምና የጸጥታ ማዕቀፉ በአስቸኳይ እንዲደራጅ ጠይቀዋል፡፡