በሀያት ታህሪር አልሻም የሚመሩት የሶሪያ አማጺያን በፈጸሙት መብረቃዊ ጥቃት ለ 50 አመታት የቆየውን የአሳድ ቤተሰባዊ አስተዳደር ገርስሰዋል
የሩሲያ የልኡክ ቡድን አሳድ ከወደቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶሪያ ደማስቆ ደርሷል።
የሩሲያ የልኡክ ቡድን የሞስኮ አጋር የሆኑት ፕሬዝደንት በሽር አልአሳድ ከስልጣን ከወደቁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው እለት ደማስቆ መግባቱን ሮይተርስ የሩሲያውን ታሶ የዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
ሩሲያ በሶሪያ ያለው የጦር ሰፈሯ እንዳይነካበት ጥረት እያደረገች ነው።
ከሶሪያ አዲሶቹ መሪዎች ጋር ንግግር ያደርጋል የተባለው የልኡክ ቡድን የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚክኤል ቦግዳኖቭንና የክሬሚሊንን የሶሪያ ልዩ መልእክተኛ አሌክሳንደር ላቭሬንቲቭን ማካተቱን ዘገባው ጠቅሷል።
ሁለት የሶሪያ ምንጮች በሩሲያ የልኡክ ቡድንና በሶሪያ አመራር መካከል በዚህ ሳምንት ንግግር ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለሮይተርስ ቀደም ብለው ተናግረዋል።
ለአሳድ ጥገኝነት የሰጠችውና ከመውደቁ በፊት ከአማጺያኑ ጋር በሚያደርገው ጦርነት ወታደራዊ ድጋፍ ስታደርግለት የነበረችው ሩሲያ ሶሪያ ውስጥ በታርቶስ ያለው የባህር ኃይሏና በወደብ ከተማዋ ታላኪያ አቅራቢያ ያለው ሀሚሚም ያለው የአየር ኃይሏ ባለበት እንዲቆይ ትፈልጋለች።
የታርቶስ ጣቢያ የሩሲያ ብቸኛው የሜዲትራኒያን የጥገና የማደሻ ማዕከል ነው። ሞስኮ የጦር ኃይሏን ወደ አፍሪካ ለማስገባትና ለማስወጣት ሶሪያን እንደመነሻ ትጠቀማለች።
በሀያት ታህሪር አልሻም የሚመሩት የሶሪያ አማጺያን በፈጸሙት መብረቃዊ ጥቃት ለ 50 አመታት የቆየውን የአሳድ ቤተሰባዊ አስተዳደር ገርስሰዋል።