በመጀመሪያው ዙር ከሚለቀቁ ታጋቾች ውስጥ ስምንቱ በሀማስ መገደላቸውን እስራኤል አስታወቀች
ከሀማስ ጋር በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ከሚለቀቁት 26 ታጋቾች መካከል ነው ስምንቱ መሞታቸው የተሰማው
የእስራኤል መንግስት ለሞቱ ታጋች ቤተሰቦች ሁኔታውን ማሳወቁን ገልጿል
በዛ የተኩስ አቁም ስምምነት በመጀመሪያው ምዕራፍ በሃማስ ከሚለቀቁ 26 ታጋቾች መካከል ስምንቱ መሞታቸውን እስራኤል ገልጻለች።
የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ዴቪድ ሜንሰር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት እስራኤል የታጋቾቹን ሁኔታ የሚገልጽ ዝርዝር ከፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ደርሷታል።
ቃል አቀባዩ ሞተዋል የተባሉትን ታጋቾች ስም ዝርዝር ባላሳወቁበት መግለጫቸው ሁኔታውን ለሟቾች ቤተሰብ መንግስት ማሳወቁን ተናግረዋል፡፡
የተኩስ አቁም ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ ሰባት ሴት ታጋቾች ሲለቀቁ በተመሳሳይ ወቅት በእስራኤል እስር ቤቶች የታሰሩ ከ290 በላይ ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለቀዋል።
እሁድ ምሽት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ፅህፈት ቤት ሃማስ አንድ ሴት ወታደረን ጨምሮ ሶስት ታጋቾችን ሐሙስ ዕለት ለመልቀቅ መስማማቱን እና ሶስት ተጨማሪ ታጋቾችን ደግሞ በመጪው ቅዳሜ እንደሚለቅ ማሳወቁን ይፋ አድርጓል።
ከታጋቾቹ መካከል 87ቱ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን 34ቱ ሞተዋል ተብሏል፤ በተጨማሪም ከጦርነቱ በፊት ታፍነው ከተወሰዱት ሶስት እስራኤላውያን መካከል አንደኛው መሞቱን የመንግስት ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ቅዳሜ እለት፣ በሁለተኛው የተኩስ አቁም ልውውጥ አራት ሴት የእስራኤል ወታደሮች መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ የሶስት ታጋቾች ደህንነት በጣም አሳስቦኛል ብሎ ነበር፡፡
ከሞቱ ታጋቾች ጋር በተያያዘ ሀማስ ታጋቾቹ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት መገደላቸውን ሲገልጸ እስራኤል በበኩሏ በሀማስ እጅ መገደላቸውን ትገልጻለች፡፡
ተጨማሪ እስረኞች መፍታት፣ የቀሩ ታጋቾች እንዲለቀቁ ፣ ሙሉ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሰርጥ እንዲወጣ እና ዘላቂ መረጋጋት እንዲሰፍን የሚጠይቀው ሁለተኛው ዙር ድርድር በየካቲት 4 ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል ።
ሶስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ሁሉንም ታጋቾች ማስለቀቅ አመታት ሊወስድ የሚችለውን የጋዛን መልሶ ግንባታ ማስጀመርን ያካትታል።
የታጋቾች እና የጠፉ ቤተሰቦች ፎረም የእስራኤል መንግስት ሶስቱንም ደረጃዎች ተግባራዊ እንዲያደርግ እና ሁሉም ታጋቾች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እየጠየቀ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡