ኢትዮጵያን ጨምሮ 9 የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የአለም አቀፍ ጎብኝዎች መዳረሻ መሆናቸው ተገለጸ
ሀገራቱ በ2023 50 ሚሊየን የሚጠጉ ጎብኝዎችን ማስተናገድ ችለዋል ነው የተባለው
በ2024 9 ወራት ብቻ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ1ቢሊየን በላይ ሰዎች የጉብኝት ጉዞዎችን አድርገዋል
የአፍሪካ ቱሪዝም ሴክተር በከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ እንደሚገኝ ትራቭል ኤንድ ቱር ወርልድ የተባለው ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
አለም አቀፋዊ የቱሪዝም መዳረሻቸዎችን እና ደረጃዎችን የሚያወጣው ድረገጹ ኢትዮጵያ ፣ ግብጽ ፣ ሞሮኮ ፣ቱኒዚያ ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ታንዛኒያ ፣ ሞሪሽየስ ፣ ሲሽየልስ እና ስዋቲኒ በአህጉሪቷ ቀዳሚ የቱሪስ መዳረሻ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡
እነዚህ መዳረሻዎች በጋራ ከ50 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎችን የተቀበሉ ሲሆን ይህም ለአፍሪካ የጉዞ ኢንዱስትሪ መሻሻል ትልቅ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
እያንዳንዳቸው ሀገራት ልዩ የተፈጥሮ መስህቦችን ፣ ባህል ፣ ቅርሶችን እና ዘመናዊ መስህቦች መገኛ መሆናቸው ከመላው ዓለም ተጓዦችን እንዲስቡ አስችሏቸዋል፡፡
እንደ ግብፅ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዚያ ያሉ ሀገራት የአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት ማዳረሻ ሲሆኑ እንደ እስዋቲኒ እና ሲሼልስ ያሉ ትናንሽ ሀገራት ደግሞ የአለምን ትኩረት እየሳቡ ነው።
በ2024 የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 1.1 ቢሊዮን ቱሪስቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ለጉብኝት ተጉዘዋል፤ በአመቱ የአፍሪካ የቱሪዝም ዘርፍ ከ2019 ጋር ሲነፃፀር የ6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
14.9 ሚሊየን ጎብኝዎችን በ2023 የተቀበለችው ገብጽ በአህጉሩ ከሚጠቀሱ የቱሪዝም ማዳረሻዎች መካከል ቀዳሚዋ ናት፡፡
የጊዛ ፒራሚዶች፣ ሰፊኒክስ እና የሉክሶር ቤተመቅደሶችን ጨምሮ የሀገሪቱ ጊዜ የማይሽረው ድንቅ ታሪካዊ መስህቦች ቀዳሚ የጎብኝዎች አይን ማረፋያዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ግብፅ በቀይ ባህር ዳርቻዎች ላይ የገነባቻቸው እንደ ሻርም ኤል ሼክ እና ሁርጋዳን የመሳሰሉ ሪዞርቶች ከታሪካዊው ጉብኝት አለፍ ብሎ ቅንጡ የጉብኝት አለምን የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል።
ከ2024 መጀመርያ አንስቶ ግብፅ ከ112 ሀገራት ለሚመጡ ዜጎች ከቪዛ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በሯን ከፍታለች፤ ይህ እርምጃ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እና ከተለያዩ የአለም ክፍሎች ለሚመጡ ጎብኚዎች መሰህቦቿን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ አግዟታል።
14.52 ሚሊየን ጎብኝዎች የጎበኟት ሞሮኮ ግብጽን በመከተል ሁለተኛ ስትሆን ቱኒዝያ 9.37 ሚሊየን ፣ ደቡብአፍሪካ 8.5 ሚሊየን ጎብኝዎችን በመቀበል በደረጃ ይገኛሉ፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተችው ኢትዮጵያ 1.08 ሚሊየን አለም አቀፍ ጎብኝዎችን እንዳስተናገደች ተገልጿል፡፡
የበለጸገ ባህል ፣ ታሪክ እና ቅርጽ ባለቤት መሆኗ በሚነገርላት ኢትዮጵያ ጎብኚዎች የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ጥንታዊቷ የአክሱም ከተማ እና አስደናቂውን የስሜን ተራሮች ለማየት ያቀናሉ፡፡
በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚገኙ የቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን ፣ የመርካቶ ገበያ እና በመዲናዋ የሚገኙ ሙዝየሞች እንዲሁም የጎንደር ቤተ መንግስቶች ወደ ኢትዮጵያ ለሚሄዱ ጎብኝዎች ተጨማሪ አይን ማረፍያ ናቸው ተብሏል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ፣ የደቡብ አሜሪካ የእስያ እና የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ ለ90 ሀገራት ከቪዛ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፈቅዳለች፡፡