የታይም መጽሄት የ2024 የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ማን ነው? ትራምፕ ወይስ ኔታንያሁ?
ታይም ከ1927 ጀምሮ በአለማችን በበጎም ይሁን በመጥፎ ተጽዕኗቸው ጉልህ የነበሩ ሰዎችን እየመረጠ ይፋ ያደርጋል

ዶናልድ ትራምፕ በ2016 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን እንዳሸነፉ የታይም የአመቱ ሰው ተብለው መመረጣቸው ይታወሳል
የአሜሪካው ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዶናልት ትራምፕ በታይም መጽሄት የ2024 የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪው ሰው ተብለው መመረጣቸው እየተነገረ ነው።
ፖለቲኮ ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ትራምፕ የታይም የአመቱ ሰው ተብለው መመረጣቸውን ተከትሎ የኒውዮርክ የአክስቲዮን ገበያ የመክፈቻ ደወል በዛሬው እለት ይደውላሉ።
ሪብሊካኑ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ወደ ፖለቲካው መድረክ ከመቀላቀላቸው በፊት በኒውዮርክ የሪልስቴት አልሚ ነበሩ።
በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸውም ስኬታቸውን በአክሲዮን ገበያው ጥንካሬ መሰረት ይመዝኑ ነበር ያለው ሬውተርስ፥ የአክሲዮን ገበያው የሚጀመረውም ሆነ የሚጠናቀቀው በደወል እንደመሆኑ ደወሉን መደወል ልዩ ክብር እንደሚሰጠው አመላክቷል።
40ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን፣ የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እና ታዋቂው ተዋናይ አርኖልድ ሽዋዚንገር ደወሉን ከደወሉ ጥቂት ሰዎች ውስጥ እንደሚገኙበትም ነው ያወሳው።
ሲኤንኤንን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ትራምፕ በመጽሄቱ የአመቱ ሰው ተብለው መመረጣቸውን ቢዘግቡም ታይም እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
የአሜሪካው ታዋቂ መጽሄት ትራምፕ በ2016 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳሸነፉ የአመቱ ሰው የሚለውን ክብር ሰጥቶ በፊት ገጹ ይዞ መውጣቱ የሚታወስ ነው።
ትራምፕን አሽንፈው ዋይትሃውስ የዘለቁት ጆ ባይደን እና ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ በ2020 ፤ የፖፕ ሙዚቃ ኮከቧ ታይለር ስዊፍት ባለፈው አመት የታይም የአመቱ ሰው መባላቸው አይዘነጋም።
ታይም መጽሄት ተደጋጋሚ ትችት ሲያነሱበት የቆዩትን ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የአመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ብሎ ይፋ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው ዛሬ ነው።
መጽሄቱ ከ1927 ጀምሮ በአለማችን በ12 ወራት ውስጥ በበጎም ይሁን በመጥፎ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሰዎችን እየመረጠ ይፋ ያደርጋል።
በዚህ አመትም ከመጨረሻ አስር ውስጥ ከገቡት መካከል ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ፣ ቢሊየነሩ ኤለን መስክ፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበግ ይገኙበታል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በ2022 ፤ ኤለን መስክ በ2021 ፤ የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ደግሞ በ2012 እና 2018 በታይም መጽሄት የአመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ መባላቸው ይታወሳል።