ህብረቱ ባሳለፍነው ዓመት የእስራኤል ልኡካንን ከመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ማባረሩ ታወሳል
የአፍሪካ ህብረት ሳይጋበዙ ጉባኤውን ለመሳተፍ የሚመጡ ሰዎችን አስጠነቀቀ፡፡
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የሚሳተፉበት 44ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ለሚመጡ ታዛቢ ሀገራት ማስጠንቀቂያ አውጥቷል፡፡
ህብረቱ ባወጣው መግለጫ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተጋበዙ ሀገራት እና ተቋማት ውጪ የሚመጡ ተሳታፊዎችን እንደማያስተናግድ አስጠንቅቋል፡፡
37ኛው የህብረቱ መሪዎች እና 44ኛው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤን በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው ሀገራት እና ተቋማት ውጪ እንዳይመጡ እና ፈቃድ የተሰጣቸው ደግሞ ከአንድ ተወካይ በላይ እንዳይመጡ ሲልም ህብረቱ አሳስቧል፡፡
ከዚህ በፊት በአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎች ላይ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ፈቃድ የተሰጣቸው ሀገራት እና ተቋማትም ፈቃዳቸውን እንዲያድሱ ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በተካሄደው 43ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ እስራኤል በዚህ ጉባኤ ላይ እንድትሳተፍ ፈቃድ አልተሰጣትም በሚል በወቅቱ ቴልአቪቭን ወክለው በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የነበሩት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ሳሮን ገብስ ከስብሰባው አዳራሽ በጸጥታ ሀይሎች መባረራቸው ይታወሳል፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የእስራኤል ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የመክፈቻ ስነስርዓት አልተሳተፈም።
አማርኛ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጠየቀች
እስራኤል ይህን ያደረጉት ደቡብ አፍሪካ እና አልጄሪያ ናቸው ስትል የወቀሰች ሲሆን ሚኒስቴሩ በመግለጫው ይህ ክስተት እጅግ አደገኛ ነው፣ እስራኤል የአፍሪካ ህብረት እንደ አልጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሀገራት እጅ ወደ “ታጋችነት” መቀየሩ አሳዛኝ ነው ስትል ክስተቱን ተችታለች።
አፍሪካ ህብረት ከ50 በላይ የዓለም ሀገራትን በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን ከ10 በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በተመሳሳይ በታዛቢነት በየዓመቱ ይሳተፋሉ፡፡
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ካናዳ፣ ብራዚል፣ ጀርመን፣ ህንድ እና ሌሎች ሀገራት የሕብረቱን ጉባኤዎች በታዛቢነት እንዲሳተፉ ፈቃድ ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት ስር ያሉ እና ሌሎች የሰብዓዊ ልማት ተቋማትም በህብረቱ ጉባኤዎች ላይ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው ተቋማት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡