ፖለቲካ
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ደረሱ በተባሉ የመብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ልጀምር ነው አለ
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ምርመራ የፊታችን ሀሙስ ሰኔ 10 2013 በይፋ ይጀምራል
ኮሚሽኑ ለ3 ወራት በሚያካሂደው ምርመራው በትግራይ ክልል መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ እንደሚመለከት አስታውቋል
የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ተባሉ የመብት ጥሰቶችን በይፋ መመርመር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ምርመራ የፊታችን ሀሙስ ሰኔ 10 2013 በይፋ እንደሚጀምርም አል ዐይን በዛሬው እለት ከኮሚሽኑ ያገኘው መግለጫ ያመላክታል።
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ ሥራውን በጋምቢያዋ ዋና ከተማ ባንጁል በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ እንደሚጀምርም አስታውቋል።
በዚህም መሰረት በትግራይ ክልል መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ እንደሚመረምር የገለጸ ሲሆን፤ አስፈላጊ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላም የጎረቤት ሀገራትን ሁኔታ ለማየት እንደሚሞክር ነው የገለጸው።
ኮሚሽኑ ለሶስት ወራት ተቀምጦ ሁኔታውን እንደሚመረምር የገለጸ ሲሆን፤ የሶስት ወራት ጊዜውም ሊታደስ እንደሚችልም ነው የተገለጸው።
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን የመብት ጥሰቶችን የመመርመር ኃላፊነት እንዳለውም ገልጿል።