የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዕድል ወይስ ፈተና?
እ.ኤ.አ. ጥር 1/2021 ተግባራዊ የሆነውን ስምምነቱን ከኤርትራ በቀር 54 አባል ሀገሮች ፈርመው ተቀብለውታል
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ለውውጥ በ14 ቢሊዮን ዶላር ይጨምራል ተብሏል
አፍሪካን በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም የማዋሃድ ተልዕኮ ያነገበው አህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ የኢትዮጵያን ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች መሪዎችም ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ነጻ የንግድ ቀጠናው በአፍሪካ ሀገራት መካከል ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ በአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲመጣ፣ የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ እንዲያድግ፣ ለስራ ፈጠራ እና ሚዛናዊ የንግድ ስርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
በድርድሮች መጓተትና በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተግባራዊነቱ ዘግይቶ የነበረው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ጥር 1 ቀን 2021 ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ በአየር መንገዷ በኩል በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚጓጓዘውን የመጀመሪያ ጭነት ከእስዋቲኒ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ጀምራለች፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ለግሉ ዘርፍ ያለው ዕድልና ተግዳሮት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ነጻ የንግድ ቀጠናው በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ በ 20 በመቶ ወይም በ14 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጨምረው ገልጸዋል፡፡
በንግድ ሚኒስቴር የባለብዙ ወገን ንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ ነጻ የንግድ ቀጠናው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ አምራቾች ተገማችና ሰፊ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡ ‘አጎአ’ን (AGOA) የመሳሰሉ ለአፍሪካ የተሰጡ የንግድ አማራጮች ቢኖሩም ዘላቂ ባለሀመሆናቸው ይህ የንግድ ስምምነት ግን ዘላቂና አስተማማኝ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ብዙ እንደምትጠቀም ያነሱት ዳይሬክተሩ በአግባቡ ከተጠቀመች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በአፍሪካ ደረጃ ያለው የመሰረተ ልማት ሁኔታ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ፈተና እንደሚሆን በርካቶች በተደጋጋሚ አንስተዋል፡፡ አቶ ሙሴ ምንዳዬ በአፍሪካ ያለው የመሰረተ ልማት ሁኔታ አስቸጋ ቢሆንም በተለያዩ ቦታዎች እየተሰሩ ያሉ የባቡር መሰረተ ልማቶች መኖራቸው ችግሩን እንደሚያቀለው አንስተዋል፡፡ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን በተመለከተ ነጋዴዎችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች መረጃ ደርሷቸዋል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በንግድና ዘርፍ ማህበራት በኩል መረጃው ተደራሽ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና በቀጣይ ይህንን በተመለከተ የተደራጀ መረጃ የመስጠት ሂደት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ጥር 2013 ዓ.ም ወደ ስራ የገባውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ከኤርትራ በቀር 54 አባል ሀገሮች ፈርመው ተቀብለውታል፡፡