ኢትዮጵያ የአንድ ሰው ዕድሜ ያስቆጠረውን የንግድ ህግ በአዲስ ልትተካ ነው
“ህጉ ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል”-መላኩ አለበል፣የንግድ ሚኒስትር
ህጉ ያለፉትን 60 ዓመታት አገልግሏል
ኢትዮጵያ የአንድ ሰው ዕድሜ ያስቆጠረውን የንግድ ህግ በአዲስ ልትተካ ነው
በተለያዩ ሃገራዊ አጀንዳዎች ላይ ተወያቶ ውሳኔዎችን ያሳለፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 85ኛ መደበኛ ስብሰባ ከ60 ዓመታት በፊት የወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ህግ በአዲስ እንዲተካ ወስኗል፡፡
በ1952 ዓ/ም የወጣው ህጉ ከወጣበት ዘመን አንጻር ከጊዜው የቀደመ ነበር ለማለት ይቻላል ያለው ምክር ቤቱ ባለፉት 60 ዓመታት በርካታ የንገድ ጉዳዮች መለዋወጣቸውን እና ህጉ ለአፈጻጸም የማይመቹና ለተለያዩ ትርጉሞች የተጋለጡ ብዙ ድንጋጌዎችን ስለመያዙ በጥናት ተረጋግጧል ብሏል፡፡
ለመጪዎቹ አስርት ዓመታት የሚታሰበውን የሃገሪቱን የንገድ እንቅስቃሴ ለመምራት ካለማስቻልም በላይ ዛሬ ኢትዮጵያ ለደረሰችበት የኢኮኖሚ ደረጃም ቢሆን የተሟላና በቂ ሆኖ አለመገኘቱን ገልጿል፡፡
በመሆኑም በምክር ቤቱ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው፡፡
የአንድ ሰው ዕድሜ ያስቆጠረውን የንግድ ህግ የሚተካ 2ኛው የንግድ ህግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን የተመለከተ ጽሁፍን በግል የትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል “ህጉ ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል” ብለዋል፡፡
የህጉ በአዲስ መተካት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ይጠበቃል፡፡
የኮርቤቲ እና ቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ፕሮጄክቶችን በተመለከቱ የማስፈጸሚያ ስምምነቶች ላይ ይሁኝታውን የሰጠው ምክር ቤቱ የማዕድን ስራዎች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያቶ ወደ ምክር ቤት የመራ ሲሆን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡