ኢትዮጵያ የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን በይፋ አስጀመረች
የሃገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ ከማቀላጠፍ ባለፈ በኢንቨስትመንት ፍሰት እና በስራ እድል ፈጠራ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ታምኖበታል
አገልግሎቱ ዛሬ በተካሄደ ይፋዊ የማብሰሪያ ስነ ስርዓት ተመርቆ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል
ኢትዮጵያ የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት የአሰራር ስርአትን ይፋ አደረገች፡፡
የበይነ መረብ የአሰራር አገልግሎቱ ዛሬ በይፋ መጀመሩን የሚያበስር ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የአገልግሎቱን በይፋ ስራ መጀመር አስመልክተው ንግግር ያደረጉት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት ኢትዮጵያ በንግድ ምቹነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሃገራት መካከል ናት፡፡
አዲስ የሚጀምረው አገልግሎት ንግድ ፍቃድ ለማውጣት የሚወስደውን ጊዜ እና ገንዘብ ይቀንሳል ያሉት ሚኒስትሩ መደበኛ የንግድ ስራን ያበረታታል፣ ሙስናን ይከላከላል በንግድና ኢንቨስትመንት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል፡፡
ዘመናዊ እና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያግዝም ነው የገለጹት፡፡
አቶ መላኩ ንግድን ማዘመን ሰፊ የስራ ዕድልን የመፍጠር፣ የሸማቾችን መብት የማስጠበቅ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ነው ያሉም ሲሆን የጥቂት ሃገራትን ተሞክሮ በማንሳት በቂ የአመራር ትኩረት ከተሰጠው ምናልባትም ቀድሞ ከታሰበለት ተጠናቆ ሊሳካ እንደሚችል አሳይተዋል፡፡
አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በሃገራችን በኋላቀር አሰራራቸው ሊጠቀሱ ከሚችሉት አንዱ የንግድ ስርዓታችን ነው ብለዋል፡፡
የእድሜውን ያህል ሊሻሻል አልቻለም ያሉም ሲሆን ሊዘምንና የተወዳዳሪነት አቅሙ ሊያድግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡
ለዚህም በመንግስት በኩል የንግድ ስርዓቱን ከመሰረቱ ለመለወጥ የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ነው አቶ ደመቀ ያሉት፡፡
ሃገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያዎችን በማሳያነትም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በያዝነው ወር ወደ ስራ የገባውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትንም ፈርማለች፡፡
የአገልግሎቱ መጀመር በእነዚህ እና በሌሎችም መንገዶች ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የሚያስችል ነው ሲሉም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት፡፡
የአንድ ጤናማ ሰው ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የንግድ ህግ ከ60 ዓመታት በኋላ ባሳለፍነው ሰኔ በአዲስ እንዲተካ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡