የመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድ የሆነባቸው የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የህዝብ ቁጥር መጨመርና የከተሜነት መስፋፋት ለመኖሪያ ቤት ዋጋ መናር መንስኤ ናቸው
ካሜሮን፣ ኢትዮጵያና አልጄሪያ ከአፍሪካ በመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድነት ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል
የህዝብ ቁጥር እየሰፋ ሲሄድ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ መናር ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራትም በህዝብ ቁጥር መጨመር፣ በኢኮኖሚ እድገት እና በፈጣን የከተሞች መስፋፋት ላይ ሲሆኑ፤ ይህም ለመኖሪያ ቤት ዋጋ መናር መንስኤ እየሆነ መጥቷል።
በዓለም ዙሪያ የኑሮ ደረጃዎችን የሚከታተለው ነምቤኦ የተባለ ድርጅት፤ በ2024 በአፍሪካ ሀገራት ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ ዝርዝር ይፋ አደርጓል።
ነምቤኦ ያወጣው ሪፖርት በየጊዜው ተለዋለዋጭ ሲሆን፤ ሪፖርቱ የሀገራቱን ዜጎች ገቢ እና የመኖሪያ ቤቶችን ዋጋ ጥምርታን በማነጻጸር የተሰራ እንደሆነም አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ከአፍሪካ የመኖሪያ ቤት ዋጋ በጣም ውድ በመባል ካሜሮን 1ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ ከዓለም 2ኛ ደረጃን ይዛለች፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 43.9 በመቶውን እንደሚሸፍንም ተመላክቷል።
በሪፖርቱ ኢትዮጵያ በመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድነት ከአፍሪካ 2ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 43.1 በመቶውን እንደሚሸፍንም ተመላክቷል።
አልጄሪያ በመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድነት ከአፍሪካ 3ኛ ከዓለም ደግሞ 21ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 17.4 በመቶውን እንደሚሸፍንም ሪፖርቱ አመላክቷል።
ሞሮኮ ከአፍሪካ 4ኛ ከዓለም ደግሞ 26ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 15.9 በመቶውን እንደሚሸፍንም ነው የተገለጸው።
በመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድነት ከአፍሪካ 5ኛ ከዓለም ደግሞ 31ኛ ደረጃ ለይ የተቀመጠችው ግብጽ ስትሆን፤ የግብጽ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 15.3 በመቶውን ይሸፍናል ተብሏል።
ቱኒዝያ ከአፍሪካ 6ኛ ከዓለም ደግሞ 43ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 13.1 በመቶውን ይይዛል።
ጎረቤት ሀገር ኬንያም ከአፍሪካ 7ኛ ከዓለም ደግሞ 47ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 12.1 በመቶውን ይሸፍናል ነው የተባለው።
በሪፖርቱ ላይ የተካተተችው ደቡብ አፍሪካም ከአፍሪካ 8ኛ ከዓለም 103ኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን፤ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 3.4 በመቶውን እንደሚሸፍንም ሪፖርቱ አመላክቷል።
ነምቤኦ ረፖርት መሰረት በዓለም የመኖሪያ ቤት ዋጋ በጣም ውድ የሆነባት ሀገር ሶሪያ ስትሆን፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 101.9 በመቶ እንደሆነም ተገልጿል።