ቤት ከመከራየት “በአውሮፕላን እየተመላለሱ” መማር የሚሻልባት የካናዳ ከተማ
በሳምንት ሁለት ጊዜ በአውሮፕላን እየተመላለሰ የሚማር የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጪ መቀነስ እንደቻለ ይናገራል
ተማሪው በወር ለትራንስፖርት 1 ሺህ 200 ዶላር ያወጣል ተብሏል
የካናዳው ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጪ ለመቀነስ የዘየደው መላ አነጋጋሪ ሆኗል።
ቲም ቼን የተባለው ተማሪ በቫንኮቨር ከተማ ቤት ከመከራየት ይልቅ በአውሮፕላን እየተመላለሱ መማር የተሻለ ነው ብሏል።
የካሊግሪ ነዋሪው ቼን በሳምንት ሁለት ቀን (ማክሰኞና ሃሙስ) ወደ ቫንኮቨር በአውሮፕላን ሄዶ በመመለስ ትምህርቱን እየተካተታለ መሆኑን ገልጿል።
ወርሃዊ የቤት ኪራይ ከመክፈል የአየር ትራንስፖርቱ ወጪ ይቀንሳል በሚል ረዲት ላይ ያሰፈረው ጽሁፍም በርካቶች አስተያየት ሰጥተውበታል።
ቼን ለደርሶ መልስ 150 ዶላር ያወጣል፤ በወር 1 ሺህ 200 ዶላር እንደማለት ነው።
በቫንኮቨር ከተማ ባለ አንድ መኝታ ቤት ለመከራየት በጥቂቱ 2 ሺህ 100 ዶላር ያስፈልጋል። የምግብና ሌሎች ወጪዎች ሲደመሩም ከባድ ይሆናል የሚለው ቼን ጠዋት ወጥቶ ማታ መመለስን መርጧል።
በካሊግሪ ከቤተሰቦቹ ጋር እንደመኖሩም በቫንኮቨር ቤት ተከራይቶ ከመኖር በሳምንት ሁለት ቀን በአውሮፕላን መመላለሱ ብዙ ገንዘብ አድኖልኛል ባይ ነው።
አንድ አስተያየት ሰጪ “የዘመኑ ችግር ዘመናዊ መፍትሄ ይፈልጋል፤ ቼን ያደረገውም አስተማሪ ነው” ብሏል።
ሌላኛው ደግሞ “አንድ ስአት በማይሞላ በረራ እየተመላለሱ ትምህርትን መከታተል ያን ያህል ከባድ ባይሆንም በየጊዜው ወደ አውሮፕላን ማረፊያ መመላለስ ግን አሰልቺ” ይሆናል ሲል ሃሳቡን አጋርቷል።
“የዚህ ተማሪ ጸሎት በረራ እንዳያልፈውና እንዳይሰረዝ ነው” የሚል አስተያየትም ሰፍሯል።
በርካቶች ግን ተማሪው ለኑሮ ከበድ ትላለች በተባለችው ቫንኮቨር ወጪን ለመቀነስ የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን ነው ያነሱት።