በአፍሪካ በርካታ ድሮኖችን የገዙ 10 ሀገራት (1980 - 2024)
ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ናይጀሪያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድሮን በመግዛት ቀዳሚ ናቸው ተብሏል
ባለፉት አስርት አመታት ድሮንን ለውጊያ የሚጠቀሙ ሀገራት ቁጥር በአራት እጥፍ ማደጉን የሚሊታሪ አፍሪካ ድረገጽ መረጃ ያሳያል
ሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ከቅኝት ግልጋሎት ተሻግረው ቦምብ መጣል ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል።
ከዩክሬን እስከ ሶሪያ፣ ከየመን እስከ ሳህል ቀጠና፣ ከሩሲያ እስከ ምስራቅ ቻይና ባህር ያልተሰማሩበት የውጊያ ስፍራ የለም ማለት ይቻላል።
ባለፉት አስርት አመታት ድሮንን ለዘመናዊ ውጊያ የሚጠቀሙ ሀገራት ቁጥር በአራት እጥፍ ማደጉን የሚሊታሪ አፍሪካ ድረገጽ መረጃ ያሳያል።
ድሮኖች በአፍሪካም ከቅኝትና ሎጂስቲክ ከማመላለስ ባሻገር በውጊያ ሜዳ ላይ ወሳኝ ድርሻ እየያዙ ነው።
በሳህል ቀጠና እንደ ቦኮ ሀራም እና ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖችን እንቅስቃሴ ከአየር ላይ ምስል አንስቶ በፍጥነት ጥቃት ለማድረስ የድሮኖች ሚና ከፍተኛ ሆኗል።
ይሁን እንጂ ድሮኖች የበርካታ ንጹሃንን ህይወት መቅጠፋቸው በውጤታማነታቸው ላይ ጥያቄ እንዲነሳባቸው ያደርጋል።
ሚሊታሪ አፍሪካ ድረገጽ 31 የአፍሪካ ሀገራት ከ1980 እስከ 2024 ምን ያህል ድሮኖችን ገዝተዋል? ዝርዝር መረጃቸውስ ምን ይመስላል የሚለውን ጥናት አድርጎ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
ሀገራቱ በ34 አመታት ውስጥ 1 ሺህ 534 ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውሉ ድሮኖች መግዛታቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።
ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ናይጀሪያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድሮን በመግዛት ቀዳሚ ናቸው ያለው ሚሊታሪ አፍሪካ፥ ኢትዮጵያን አራተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።