ያለሰው እርዳታ ኢላማቸውን በራሳቸው መርጠው የሚያጠቁ አውቶማቲክ ድሮኖች
የአሜሪካው ኤሮቫይሮመንት የሚያመርታቸው “ስዊችብሌድ” ድሮኖች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ኢላማ ለይተው ጥቃት ያደርሳሉ
እነዚህ ድሮኖች ኢላማ ስተው ሊያደርሱት የሚችሉት ጥፋት ግን አሁንም ድረስ አከራካሪ ነው
ድሮኖች በተለያዩ የአለማችን ሀገራት የተካሄዱ ጦርነቶችን መልክ እየቀየሩ ነው።
ከአፍጋኒስታን እስከ ሊቢያና ዩክሬን ጥቅም ላይ የዋሉት ድሮኖች የጠላትን ኢላማዎች በመምታት የተለመደውን የመድፍና የክላሺንኮቭ ፍልሚያ ከንቱ ማድረግ ጀምረዋል።
ድሮኖች ከብዙ ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሰዎች ቁጥጥር እየተደረገባቸው የተሰጣቸውን ኢላማ መተው መመለስ መቻላቸው በግዙፍ ጄቶች የሚፈጸም ድብደባ ይዞት የሚመጣውን አደጋና ኪሳራም መቀነሱ ነው የሚነገረው።
አሁን ላይ ደግሞ ያለማንም የሰው ልጅ ድጋፍ ኢላማቸውን ለይተው መምታት የሚችሉ ድሮኖች ተሰርተው አገልግሎት ላይ መዋል መጀመራቸውን ቢዝነስ ኢንሳይደር አስነብቧል።
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ድሮኖችን በማምረት የሚታወቀው የአሜሪካው ኩባንያ ኤሮቫይሮመንት፥ የሰራቸው “ስዊችብሌድ” ድሮኖች በአሁኑ ወቅት በዩክሬንና በሌሎች ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።
በራሳቸውን ሞትን ወይም ህይወትን ይወስናሉ የተባለላቸው “ስዊችብሌድ” ድሮኖች በሁለት አማራጭ ለገበያ ይቀርባሉ፤ “ስዊችብሌድ 300” እና “ስዊችብሌድ 600”።
“ስዊችብሌድ 300” ድሮኖች ከእጅ ክንድ ብዙም የማይተልቁ ሲሆኑ፥ ክንፋቸው ታጥፎ ማስወንጨፊያ መሳሪያ ውስጥ ይገባሉ፤ እንደ ሮኬት ሲወነጩፉም ክንፋቸውን ዘርግተው በመብረር ኢላማቸውን በራሳቸው ለይተው ይመታሉ።
6 ሺህ ዶላር የሚያወጡት “ስዊችብሌድ 300” ድሮኖች እንደ ተሽከርካሪ ያለ አነስተኛ ኢላማን ለመምታት የሚውሉ ናቸው።
ከ2 ነጥብ 5 ኪሎግራም በታች የምትመዝነው ድሮን ከተወነጨፈችበት ቦታ እስከ 15 ኪሎሜትር ድረስ ተጉዛ ኢላማዋን ትመታለች።
“ስዊችብሌድ 600” ድሮኖች ደግሞ እስከ 65 ኪሎሜትር ድረስ በመብረር ታንኮች እና ከባድ የጦር መሳሪያ ተሸካሚ ተሽከርካሪዎች ወደ አመድነት ይቀይራል ተብሎለታል።
ሚሳኤሎችን መሸከም የሚችለው “ስዊችብሌድ 600” በአጠቃላይ እስከ 55 ኪሎግራም እንደሚመዝንም የኤን ቢ ሲ ዘገባ ያሳያል።
ዘመናዊ ካሜራ፣ ጂ ፒ ኤስ እና ኢላማን የሚለዩ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም ሰዎች እና የተለየ እንቅስቃሴን የሚለይ የኮምፒውተር ፕሮግራም የተገጠመላቸው እነዚህ ድሮኖች ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም አይሰጡም።
ያለሰዎች እርዳታ የጠላትን ኢላማ በራሳቸው ለይተው ስለሚያደባዩ “ገዳይ ሮቦት” የሚሰኙት ድሮኖች ኢላማ ስተው ንጹሃንን እንዳይጎዱ ከፍ ያለ ስጋት ፈጥሯል።
“ስዊችብሌድ” ድሮኖችም ሆኑ በሰዎች ቁጥጥር የሚደረግባቸው ድሮኖች በስህተት የወዳጅ ኢላማን መተው ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ ይታያል።
አሜሪካ በተለይ በአፍጋኒስታን በፈጸመቻቸው የድሮን ጥቃቶች ከ300 በላይ ንጹሃን መገደላቸው ለዚህ በአብነት ይነሳል።
ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን ከአሜሪካ ከ700 በላይ “ስዊችብሌድ” አውቶማቲክ ድሮኖችን እንደምታገኝ ተገልጿል።
እስካሁንም ከ100 በላይ “ስዊችብሌድ” ድሮኖችን ያገኘችው ኬቭ በተለያዩ ጊዜያት ተጠቅማባቸዋለች።
“ገዳዮቹ ሮቦቶች” በሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ቁጥጥር ካልተደረገባቸው አደጋው የከፋ ይሆናል የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም ሀገራትን ያከራክራል።
ወጪያቸው ዝቅ ማለቱን በማየት ብቻ እነዚህን ድሮኖች በስፋት ጥቅም ለማዋል የሚታየው ዝንባሌ እየጨመረ መምጣቱንም ቢዝነስ ኢንሳይደር የአለማችን ቀጣዩ ስጋት ነው ብሎታል።