ኢራን ለሩሲያ ለመሸጥ ያመረተችው አዲስ ድሮን - “ሻሄድ 107”
1 ሺህ 500 ኪሎሜትሮች በመጓዝ ወታደራዊ ኢላማዎችን መቃኘትና መምታት የሚችለው “ሻሄድ 107” በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተነግሯል
ኢራንም ሆነች ሩሲያ ስለአዲሱ ድሮን ሽያጭ ማረጋገጫ አልሰጡም
ኢራን በቀጣዩ ወር ሁለተኛ አመቱን በሚይዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ድሮኖች እና ምድር ለምድር ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በማምረት ላይ ትገኛለች ተባለ።
ቴህራን “ሻሄድ 107” የሚል መጠሪያ የተሰጠው የጥቃትና ቅኝት ድሮን ወደ ሞስኮ ለመላክ መዘጋጀቷን ነው ስካይ ኒውስ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ያስነበበው።
ኢራን በልዩ ዲዛይን የተሰሩ የ”ሻሄድ 107” ድሮኖችን በ2 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ለሞስኮ ማቅረብ ሳትጀምር እንዳልቀረችም ነው የተገለጸው።
የቴህራን እና ሞስኮ ወታደራዊ ባለሙያዎች “ሻሄድ 107” እና “ሻሄድ 136” ድሮኖችን በማዕከላዊ ኢራን በሚገኝ ወታደራዊ ጣቢያ መሞከራቸውንም ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ ኢራንም ሆነች ሩሲያ ስለአዲሱ ድሮን እና የባለስቲክ ሚሳኤል ልማት እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።
“ሻሄድ 107” ድሮን ምን ልዩ ያደርገዋል?
ይህ ድሮን “ሻሄድ 101” የተሰኙ ድሮኖች ጋር የሚያመሳስለው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በልዩ ዲዛይንና አቅም የተሰራ ነው ብለዋል ለስካይ ኒውስ ሃሳባቸውን ያጋሩ ምንጮች።
የ”ቪ” ቅርጽ ያለው “ሻሄድ 107” 2 ነጥብ 5 ሜትር ርዝመት አለው፤ የክንፎቹ ርዝመት ሶስት ሜትር ይደርሳል ተብሏል።
እስከ 1 ሺህ 500 ኪሎሜትሮች መጓዝ የሚችለው ይህ ድሮን እንቅስቃሴውን በቀጥታ በቪዲዮ መከታተል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተገጥሞለታል።
ይህም የዩክሬንን ዋናዋና ወታደራዊ ይዞታዎች እና ከምዕራባውያን የተሰጧትን የሚሳኤልና ሮኬት መቃወሚያዎች በመቃኘት ጥቃት ማድረስ ያስችለዋል ነው የተባለው።
ኢራን በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ቴህራን በመቶዎች የሚቆጠሩ “ሻሄድ 131” እና “ሻሄድ 136” የተሰኙ ድሮኖችን ለሞስኮ መላኳን ሲወቅሱ ቆይተዋል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ግን “በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት አንደግፍም” በሚል ይህን ወቀሳ ማስተባበላቸው ይታወሳል።
ስካይ ኒውስ ግን ባለፈው አመት ኢራን እና ሩሲያ የተፈራረሙትን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
የኬቭ ባለስልጣናት ቴህራን በልዩ ዲዛይንና የጉዞ አቅም የተሰሩ ድሮኖችን ወደ ሞስኮ ለመላክ መዘጋጀቷ በርግጥም እውነት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የድሮኖቹን አቅም በየጊዜው የማሳደጉ ሂደት ዩክሬን እጅግ ውድ የሆኑ የአየር መቃወሚያዎችን እንድትጠቀም ያስገድዳልም ነው ያሉት።
ሩሲያ “ሻሄድ 136” ድሮኖችን ታታርሳን በተባለው ግዛት መገጣጠም መጀመሯንና በ2025 እነዚህን ድሮኖች የማምረት አቅሟ በአመት 4 ሺህ ይደርሳል የሚል ግምታቸውንም አጋርተዋል።
ቴህራን እስከ 300 ኪሎሜትሮች ምድር ለምድር የሚምዘገዘጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ለሞስኮ ለመሸጥ ወስናለች መባሉም የመልሶ ማጥቃቱ እንዳቀደችው ላልሆነላት ኬቭ ፈተና መሆኑ አይቀርም ተብሏል።