ሰባት የአፍሪካ ሀገራት በፕሬስ ነጻነት ደረጃ ከአሜሪካ እንደሚሻሉ ያውቃሉ?
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ባወጣው የ2024 የአለም የፕሬስ ነጻነት ደረጃ አሜሪካ ከ180 ሀገራት 55ኛ ላይ ተቀምጣለች
ኢትዮጵያ ካለፈው አመት 11 ደረጃዎች ዝቅ ብላ 141ኛ ደረጃን ይዛለች
በ2024 የሰባት የአፍሪካ ሀገራት የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ከአሜሪካ እንደሚሻል ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ያወጣው ሪፖርት አመላክቷል።
የፕሬስ ነጻነትን በ1791 የህገመንግስቷ አካል ያደረገችው ዋሽንግተን በአለም የፕሬስ ነጻነት ደረጃ 66.59 ነጥብ በማስመዝገብ ከ180 ሀገራት 55ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በአንጻሩ ሰባት የአፍሪካ ሀገራት ከአሜሪካ የተሻለ ነጥብ በማስመዝገብ ሚዲያ “አራተኛው መንግስት” ነው የምትለውን አሜሪካ ቀድመዋል ይላል ሪፖርቱ።
74 ነጥብ 2 ነጥብ የተሰጣት ሞሪታኒያ ከአለም 33ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች።
ናሚቢያ፣ ሲሸልስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ጋና እና ኮቲዲቯር ከ34ኛ እስከ 53ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ጋቦን፣ ሞሪሺየስ እና ጋምቢያ አሜሪካን ተከትለው 56ኛ፣ 57ኛ እና 58ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሀገራቱ ያስመዘገቡት ውጤት ባለፉት አስርት አመታት ለውጦች እየታዩ መሆኑን አመላካች ቢሆንም በበርካታ የአፍርካ ሀገራት የፕሬስ ነጻነት አሁንም አሳሳቢ ነው ብሏል ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (አርኤፍኤስ)።
የጋዜጠኞች እስርና ግድያ፣ መረጃን በነጻነት የማግኘት መብት በበርካታ የአህጉሪቱ ሀገራት አሁንም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም ሪፖርቱ ጠቁሟል።
በ2024 የአለም የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ኢትዮጵያ ካለፈው አመት 11 ደረጃ ዝቅ ብላ 141ኛ ላይ ተቀምጣለች።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የተካሄዱ ምርጫዎች በጋዜጠኞችና በፖለቲከኞች የፕሬስ ነጻነት መብት ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ነው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ያስታወቀው።
በአለም የፕሬስ ነጻነት ደረጃ 112ኛ ላይ በተቀመጠችው ናይጀሪያ 20 የሚጠጉ ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የጠቆመው ሪፖርቱ፥ በማዳጋስካር እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም ከምርጫ ጋር በተያያዘ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በነጻነት ሃሳባቸውን እንዳይገልጹ ሲዋከቡና ጥቃት ሲደርስባቸው ነበር ብሏል።
የፕሬስ ነጻነትን በማክበር በዘንድሮው ደረጃም ኖርዌይ ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን ኤርትራ ደግሞ ባለችበት የመጨረሻ (180ኛ) ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።